የምስራቅ አፍሪካ የቀጠናዊ የኃይል ትስስር የአባል ሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው! (ዶ/ር ኢንጂነር ሡልጣን ወሊ)

የምስራቅ አፍሪካ የቀጠናዊ የኃይል ትስስር የአባል ሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው! (ዶ/ር ኢንጂነር ሡልጣን ወሊ)

ሐምሌ 2፣ 2018 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ.) ኢትዮጵያ የቀጠናዊ የኤሌክትሪክ ሀይል ገበያ በይፋ እንዲጀመር ባቀረበችው ጥሪ መሠረት 37ኛው ልዩ የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር (EAPP) ስቲሪንግ ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቆ 22ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ እየተካሄደ ነው።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢንጂነር ሡልጣን ወሊ በመርሐ ግብሩ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት የምስራቅ አፍሪካ የቀጠናዊ የኃይል ትስስር የአባል ሀገራትን የኤሌክትሪክ ሀይል ትስስር ከማጠናከር ባለፈ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውንም በእጅጉ ያጠናክራል ሲሉ ተናግረዋል።

ዶ/ር ሡልጣን እንዳሉት የኢነርጂ ደህንነት የሀገር ደህንነት መሠረት ሲሆን በአባል ሀገራት መካከል የኢነርጂ ትብብርን ማሳደግ የኃይል ተደራሽነትን በተመጣጣኝ ዋጋ ከማረጋገጥ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ትስስሮችን ያጠናክራልም ነው ያሉት።

አያይዘውም በቀጣናው የኤሌክትሪክ ትስስር የተመዘገበው እድገት የብዙ ዓመታት ትጋትና የጋራ ቁርጠኝነት ውጤት ሲሆን፣ ኢትዮጵያም የተፈጥሮ ሀብቷን ወደ ታዳሽ ኃይል በመቀየር የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከል የመሆን ራዕይዋን በተግባር እያሳካች መሆኗንና ይህም በቀጣይ የአፍሪካ አቀፍ የኃይል ትስስር ለመፍጠር መሠረት እንደሚሆን አስረድተዋል።

እንዲሁም የቀጠናዊ የኃይል ገበያ ትስስርን ለማስፋፋት መሠረት የሚሆኑ የሕግ ማዕቀፎች፣ የመግባቢያ ሰነዶች፣ አስተዳደራዊ መመሪያዎችና ደንቦች ላይ የቀረቡ የማሻሻያ ረቂቆች በሰሞኑ በነበረው ስብሰባ በስፋት መነሳታቸውን የጠቀሱ ሲሆን የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻል ለቀጣናውና ለጎረቤት ሀገራት ያለውን ጥቅም በተመለከተ ያላቸውን ሀሳብ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተጠይቀዋል ።

ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ በምላሻው እነዚህ የሕግ ማዕቀፎች በአባል ሀገራት መካከል የኤሌክትሪክ ንግድን ግልጽ፣ ተጠያቂና ውጤታማ ለማድረግ፣ እንዲሁም የቀጠናውን የኃይል ትስስር በተመጣጣኝ አሠራር ለማስፈጸም በእጅጉ አስፈላጊ መሆናቸውን አብራርተው በአባል ሀገራት መካከልም የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ትብብርን የበለጠ ስለሚያጠናክሩ በጋራ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ በታሳቢነት ሊያዝ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

Share this Post