ውሃ ለሀይድሮ ፓወር፣ ለመስኖና ለመጠጥ ብቻ ሳይሆን ለሴቶችና ለልጃገረዶች በወር አበባቸው ወቅት ንፅህናቸውን በአግባቡ ለመጠበቅ የማይተካ ሚና አለው ተባለ።

ውሃ ለሀይድሮ ፓወር፣ ለመስኖና ለመጠጥ ብቻ ሳይሆን ለሴቶችና ለልጃገረዶች በወር አበባቸው ወቅት ንፅህናቸውን በአግባቡ ለመጠበቅ የማይተካ ሚና አለው ተባለ።

ሰኔ 20/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ "ለወር አበባ ንፅህና ተስማሚ የሆነች ሀገርን በጋራ እንፍጠር!" በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ለ13ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ11ኛ ጊዜ አገር አቀፍ የወር አበባ ጤና እና ንፅህና አጠባበቅ /MHH/ ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚክ ዞን በተካሄደበት መድረክ ላይ ውሃ ለሀይድሮ ፓወር፣ ለመስኖና ለመጠጥ ብቻ ሳይሆን ለሴቶችና ለልጃገረዶች በወር አበባቸው ወቅት ንፅህናቸውን በአግባቡ ለመጠበቅ የማይተካ ሚና አለው ተባለ።

በመድረኩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ወክለው የማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት አቶ ተስፋዬ ፊቻላ ሴቶችና ልጃገረዶች የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ማግኘት ከፍተኛ ተግዳሮት የሆነባቸው በርካታ ሴቶች በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ ሲሆን የወር አበባቸውን ምቹ በሆነ ሁኔታ ማስተናገድ ካለመቻል የተነሳ ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ቀሪ ማብዛትና እስከ ማቋረጥ የሚደርሱ በመሆኑ በትምህርት ተቋማትና በስራ ቦታዎች የውኃ አቅርቦት፣ የሳኒቴሽን አገልግሎቶች፣ ከዕይታ የሚከልሉና ክብርን የሚጠብቁ ቦታዎች ለማግኘት እንደሚቸገሩም ጠቁመዋል።

ሴቶች እህቶቻችን ንፅህናቸውን ለመጠበቅ ያለንፁህ ውሃ አቅርቦት የማይታሰብ ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እስካሁን በተሰሩ ስራዎች ሀገራዊ የከተማ መጠጥ ውሃ ሽፋን 84.31 በመቶና እንዲሁም የገጠር መጠጥ ውሃ ሽፋን 69.03 በመቶ ሲሆን በቀጣይ ሀገራዊ የመጠጥ ውሃ ሽፋንን በገጠርም ሆነ በከተማ 76.67 በመቶ በማድረስ በቀጣይ የሚታየውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን በመፍታት፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ ተስማሚ የሆነች ሀገር እንድትሆን ሚኒስቴር መ/ቤታችን በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ለዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚውለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ስራዎችን የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራና በቅንጅት ይሰራልም ብለዋል።

መድረኩን በይፋ የከፈቱት የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ ለሴት እህቶቻችን በቂና ጥራቱን የጠበቀ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ግብዓቶችን ለማቅረብ መሪ ቃሉ የሚጋብዝ በመሆኑ ጉዳዩ ጊዜ ስለማይሰጥ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

ዶ/ር ደረጄ አክለውም መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በጥልቀት በመረዳት በሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ላይ ተጥሎ የነበረውን ታክስ ዝቅ ማድረግ እንደተቻለ አስታውሰው፤ ችግሩ አሁንም አሳሳቢ በመሆኑ ሴቶች በወር አበባቸው ወቅት የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ የመግዛት አቅም ውስንነትን በመረዳት በሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ላይ ከታክስ ነፃ (ዜሮ %) በማድረግ ለችግሩ መፍትሄ እንደሚሰጥም እናምናለን ብለዋል፡፡

የመድረኩም ዋና ዓላማ በወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ያሉት ዶ/ር ደረጄ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግና ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይም ታክስ እንዲነሳና በቂ ግብዓት እንዲኖር ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።

የሀገራችን ሴቶች የወር አበባ ንፅህናቸውን ለመጠበቅ ከታክስ ነፃ የሆነ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ለሴቶች ምቹ የሆኑ መፀዳጃ ቤቶችን ለመገንባት ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበው ለጉባኤው መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል።

በመድረኩ የቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚክ ዞን፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ UNICEF፣ UNFPA፣ CCRDA እና የአምራቾች ዘርፍ ማህበራት ተወካዮች ባስተላለፉት መልዕክት የወር አበባ የተፈጥሮ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የትምህርት፣ የጤና፣ የስርዓተ ፆታ እኩልነት፣ የኢኮኖሚ ልማት፣ የሰብዓዊነትና የመሰረታዊ ፍላጎት ጉዳይ በመሆኑ፤ ተፅዕኖውም የሴቶችና የግለሰብ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በሀገር ላይ የሚደርስ እንደሆነ ጠቁመው ችግሩን ለመቅረፍ ወደፊት በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነትም ተፈራርመዋል፡፡

Share this Post