የኢነርጂ ዘርፍ የሚጨበጥ የተስፋ ጉዞ
የኢነርጂ ዘርፍ የሚጨበጥ የተስፋ ጉዞ
ኢትዮጵያ በታዳሽ የኃይል ምንጮች ያላት እምቅ አቅም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሽግግር እውን ለማድረግ ትልቅ ምሰሶ ነው።
በውሃ፣ በፀሐይ፣ በንፋስ እና በጂኦተርማል ሀብቶች የታደለችው ኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦቷን በማዘመን የዜጎችን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ ለቀጣናዊ ትስስር ቁልፍ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።
ኢነርጂ የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ የግብርና ምርታማነት እና የአገልግሎት ዘርፍ ዕድገት ቁልፍ ግብዓት ነው።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት "የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከል" ለመሆን በምታደርገው ጥረት የኢነርጂ መሰረተ ልማት ዝርጋታ የሀገሪቱን የሁለገብ ዕድገት ለማፋጠን ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
የኃይል አቅርቦትን አስተማማኝ እና ተደራሽ ማድረግ፣ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የግብርና ተቋማት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚደረገው ጥረት አንኳር ጉዳይ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እየተወሰዱ ካሉ እርምጃዎች ጋር አብሮ የሚሄደው የኢትዮጵያ የኢነርጂ ልማት ስትራቴጂ፣ በዋናነት በአረንጓዴ ኃይል ላይ የተመሰረተ ነው።
የሀገሪቱ የኢነርጂ ምንጭ በውሃ ኃይል ብቻ ሳይወሰን በፀሐይና በንፋስ ኃይል እንዲታገዝ የሚደረገው ጥረት የላቀ ውጤት እያመጣ ይገኛል።
ለኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የኢነርጂ ዘርፉ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ሲሆን፤ በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ትኩረት ተሰጥቷል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃት ለኢነርጂ ዘርፉ ቀጣይ ስኬት ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል።
የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት መብቃት የዘርፉን ተስፋ የሚጨበጥ አድርገውታል።
በግንባታ ላይ የሚገኘው የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በኢነርጂ ልማት ቀጣናዊ ትስስርን ለመፍጠር የጀመረችውን ጉዞ ከዳር የማድረስ ቁመና ላይ መገኘቷን ያሳያል።
በዘንድሮ በጀት ዓመት በኢነርጂ ልማትና አስተዳደር ዘርፍ የተሰሩ ስራዎች ኢትዮጵያ በዘርፉ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሷን ያመላክታሉ።
የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት መደገፍና የዜጎችን የኢነርጂ ፍላጎት የተሟላ እንዲሆን ለማድረግ የሚሰራው የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ተሻሽሏል።
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት አጠቃላይ ከተለያዩ የኃይል ምንጮች የመነጨ የኤሌክትሪክ ኃይል ከነበረበት 7,910 ሜ.ዋ ወደ 9,580 ሜ.ዋ ለማሳደግ ታቅዶ ነበር።
በዚህም 1,669 ሜ.ዋ በማመንጨት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ወደ 9,579 ማደግ ችሏል፡፡
ከሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ከውሃ ኃይል የመነጨ ኤሌክትሪክ ነው።
ከውሃ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ከነበረበት 7,451 ሜ.ዋ ወደ 9,051 ሜ.ዋ ለማሳደግ ታቅዶ በዘጠኝ ወራት 1,599 ሜ.ዋ በማመንጨት ወደ 9,050 ሜ.ዋ እንዲያድግ ተደርጓል።
በተመሳሳይ ከንፋስ ኃይል፣ ከፀሐይ እና ከጂኦተርማል የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ይገኛል።
በዘጠኝ ወራት ብቻ 45 ሜ.ዋ ከንፋስ ኃይል ማመንጨት የተቻለ ሲሆን፤ ከጸሀይ ኃይል ደግሞ 6.5 ሜ.ዋ በማመንጨት ዜጎችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደትን መደገፍ ተችሏል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ስራው ጎን ለጎንም የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ዝግጁነትን የማሳደግ ተግባር መከናወኑ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት አቅም እየተገነባ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
በአጠቃላይ በኢነርጂ ዘርፍ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ዜጎችን ተጠቃሚ የማድረግ እና ቀጣናዊ ትስስርን የማጎልበት እንቅስቃሴ ባለፉት ዓመታት ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል።
በቀጣይም የዘርፉን አቅም በማጎልበት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ፣ የከተማና ገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን እንዲሁም በኢነርጂ የቀጣናውን ሀገራት ይበልጥ ለማስተሳሰር የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።