በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ የስራ አፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ የስራ አፈጻጸም
ግምገማ ተካሄደ።
ሰኔ 1/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኢነርጂ ዘርፍ በ2018 ዓ.ም በአስር ወራት የተከናወኑ ተግባራት በክቡር ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የስብሰባ አዳራሽ በአስፈጻሚዎቹ ቀርበው ግምገማ ተካሂዶባቸዋል።
የስራ አፈጻጸም የግምገማ መድረኩን የመሩት
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ናቸው።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኢነርጂ ዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራትን በማሳለጥ ከግብ ለማድረስ የተቀረጹት የISA(International Solar Alliance),ADELE(Access to Distributed Electricity & Lighting for Ethiopia), UNDP(United Nation Development Program),
ELEAP(Ethiopia Electrification program),
ASCENT (Accelarating Sustainable and Clean Energy Transformations), Biogas ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች የትግበራ ሁኔታ እንዲሁም የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ሽግግርና የኢነርጂ ሃብት ጥናት አፈጻጸሞች በመድረኩ ለውይይት ቀርበዋል።
በአፈጻጸሙ በዋናነት በ2018 ዓ.ም ባለፉት አስር ወራት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኢነርጂ ዘርፉ የታቀዱ ዓበይት ተግባራት፣ የተጠናቀቁ፣ በሂደት ላይ ያሉትንና ያልተጠናቀቁ ተግባራት በቀጣይ ተፈጻሚ የሚሆኑበት መንገድና የነበሩ ውስንነቶችና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች በጥልቀት ተገምግመዋል።
እንዲሁም እየተሰራ ካለው ተቋማዊ የሪፎርም ስራ ጋር በተገናኘ የኢነርጂ ዘርፉ የሚታይበት ሁኔታ እንደ ሃሳብ የቀረበ ሲሆን በቀጣይ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ምላሽ የሚያገኝ እንደሚሆን ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ተናግረዋል።
ከዘርፉ ጋር በተገናኘ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያም በተለይ ግዢን ለሚጠይቁ ጉዳዮች በተቻለ መጠን ከበጀት ጋር እንዲጣጣሙ ማድረግ፣ቃል ለሚገባባቸው ስራዎች አስቀድሞ ያለው ሃብት በቂ መሆኑን መለየት፣ ውሳኔ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች ህጋዊ አካሄድን የተከተሉ እንዲሆኑ ጥንቃቄ ማድረግና ስራዎችን በጊዜ ለማጠናቀቅ ቢሮክራሲያዊ መጓተትን ማስወገድ እንደሚገባ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።
አክለውም ቀደም ሲል በአፈጻጸም ሂደት ውስንነት የተስተዋለበት ያሉትን ፕሮጀክቶችን የመከታተል አቅምን ማሳደግ፣ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድን መፈተሽና መከለስና ይጠበቃል ያሉ ሲሆን ያልተጠናቀቁ ተግባራት በቀሪ ጊዜያት ተፈጻሚ የሚሆኑበትን የጊዜ ገደብም ከአስፈጻሚዎቹ ጋር በመስማማት ውሳኔ አስተላልፈዋል።
በአጠቃላይ የነበረው አፈጻጸም በጥሩ ሁኔታ የሚታይና አበረታች ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን ክቡር ዶ/ር ኢንጂነር የገመገሙ ሲሆን በቀጣይ ዓመትም የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የዘርፉን እመርታ ለማሸጋገር ሁላችንም መትጋት ይኖርብናል ሲሉ በአጽንኦት አሳስበዋል።
በዚሁ መርኃ ግብር በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ የተቋቋሙ የፕሮጀክት አስተባባሪዎችና ሌሎች ስራ አስፈጻሚዎች የተሳተፉ ሲሆን ከመድረኩ የተሰጡ አቅጣጫዎችን በቀጣይ ተፈጻሚ ለማድረግ እንደሚረባረቡ አረጋግጠዋል።