በሰብዓዊነት የታጀበ ልማት፡ የአቅመ ደካማ ዜጎች ቤት እድሳትና ግንባታ ውጤታማ ስራዎች፡

በሰብዓዊነት የታጀበ ልማት፡ የአቅመ ደካማ ዜጎች ቤት እድሳትና ግንባታ ውጤታማ ስራዎች፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ዓመታት ያከናወናቸው የአቅመ ደካማ ዜጎች ቤት እድሳትና ግንባታ ስራዎች ከመደበኛ የልማት ፕሮጀክቶች ባሻገር ሰብዓዊ እሴትን በተግባር ያሳዩ አርዓያ ተግባራት ሆነው ተመዝግበዋል። ሚኒስቴሩ በውሃ ሀብት አስተዳደር ፣ በመጠጥ ውሃ ሳኒቴሽን ፣ በኢነርጂ እና በመሰረተ ልማት ዘርፍ ከሚያከናውናቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን ለህብረተሰቡ ያለውን ማህበራዊ ኃላፊነት በተጨባጭ በተግባር አሳይቷል። በተለይም ለአረጋውያን፣ ለአቅመ ደካማ እናቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለዝቅተኛ ገቢ ቤተሰቦች የመኖሪያ ችግር ለመቅረፍ የተደረጉ ጥረቶች የብዙዎችን ህይወት ቀይረዋል። በመላው ሀገሪቱ በተለያዩ ክልሎች የነበሩ የፈራረሱ፣ ለዝናብና ለነፋስ ተጋላጭ የሆኑ እና ለኑሮ አስጊ የነበሩ ቤቶች ተጠግነው እንዲሁም አዲስ ተገንብተው ለባለቤቶቻቸው ተረክበዋል። ከዚህ በፊት የሰው ልጅ ሊኖርበት በማይችል ሁኔታ ዝናብን እየተቀበሉ ይኖሩ የነበሩ ቤተሰቦች ዛሬ የተሻለ የመኖሪያ ሁኔታ አግኝተዋል። በቀላሉ ሊፈርሱ የሚችሉ የጭቃ ቤቶች በጠንካራ መኖሪያዎች ተተክተዋል፤ የውሃና የመብራት አገልግሎት የሌላቸው ቤቶችም መሰረታዊ አገልግሎቶችን አግኝተዋል። ይህም የተጠቃሚ ቤተሰቦችን የኑሮ ጥራት ከማሻሻል ባሻገር የስነ-ልቦና መረጋጋትና የወደፊት ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጓል። የእድሳትና ግንባታ ስራዎቹ በብዙ መልኩ ተከናውነዋል። የቆርቆሮ ቅያሪ፣ የግድግዳ ጥገና፣ የወለል ስራ፣ የበርና መስኮት ገጠማ፣ የቀለም ስራ እንዲሁም የውሃና መብራት ግንኙነት በማድረግ ብዙ ቤቶች ለመኖር ምቹ ሆነዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ አዲስ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ተሰጥተዋል። ከመኖሪያ ቤቶች በተጨማሪ የመፀዳጃ ቤት ግንባታ፣ የአካባቢ ጽዳት እና የውሃ መስመር ግንኙነት ስራዎችም ተከናውነዋል። ሚኒስቴሩ ይህ ልማት የቤት ግንባታ ብቻ ሳይሆን የተሟላ የኑሮ ሁኔታ መፍጠር መሆኑን በተግባር አሳይቷል። በእነዚህ ስራዎች ውስጥ የሚኒስቴሩ አመራሮችና ሰራተኞች ያሳዩት ተሳትፎ የሚጠቀስ ነው። በፈቃደኝነት ገንዘብ በማዋጣት፣ የግንባታ ቁሳቁሶችን በማቅረብ እና በቀጥታ በጉልበት በመሳተፍ የመረዳዳትና የአንድነት ባህልን አጠናክረዋል። ይህም መንግስታዊ ተቋማት ከህዝብ ጋር ያላቸውን ቅርበት በተግባር የሚያሳይ ምሳሌ ሆኗል። በአንዳንድ አጋጣሚዎች ለተጠቃሚ ቤተሰቦች የቤት ቁሳቁስ ፣ ፍራሽ፣ የምግብ እና የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ በማድረግ ከቤት ግንባታ ባለፈ ሰብዓዊ ድጋፍ ተደርጓል። ይህም ተጠቃሚዎቹ አዲስ ህይወት እንዲጀምሩ እና በክብር እንዲኖሩ አግዟቸዋል። በአጠቃላይ የአቅመ ደካማ ዜጎች ቤት እድሳትና ግንባታ ስራዎች ልማት ማለት ፕሮጀክትና ቁጥር ብቻ ሳይሆን የሰው ህይወትን መቀየር መሆኑን በግልጽ ያሳያሉ። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዚህ ዘርፍ ያከናወነው ስራ ለሌሎች ተቋማትም አርአያ የሚሆን ሰብዓዊ እና ልማታዊ ተግባር ነው።

Share this Post