የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል እምቅ አቅምና ተጨባጭ ተስፋ

የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል እምቅ አቅምና ተጨባጭ ተስፋ

ግንቦት 17/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ወደ ንፁህ የኃይል አማራጮች ፊቱን እያዞረ ይገኛል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ በታደለችው እጅግ ሰፊና ዘላቂ የታዳሽ ኃይል እምቅ አቅም ምክንያት በቀጣናው አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ሀገር ናት።

ከውሃ፣ ከንፋስ፣ ከፀሐይ፣ ከባዮፊውል እንዲሁም ከጂኦተርማል የሚገኘው ይህ ኃይል የሀገሪቱን የውስጥ ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር የጎረቤት ሀገራትን ትስስር የሚያጠናክር የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ምሶሶ እየሆነ መጥቷል።

በመሆኑም የኃይል ማመንጨት ሀላፊነት የተሰጠው ተቋማዊ አደረጃጀት የኢነርጂ ልማትና አስተዳደር ላይ የተለያዩ ተግባራትን በመከወን ላይ ይገኛል።

በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምን ማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል።

የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት መደገፍና የዜጎችን የኢነርጂ ፍላጎት የተሟላ እንዲሆን ለማድረግ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምን ማሻሻል የሚያስችል ስራ ተሰርቷል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከተለያዩ የኃይል ምንጮች 1 ሺህ 669 ሜ.ዋ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት 7 ሺህ 910 ሜ.ዋ የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም ወደ 9 ሺህ 579 ሜ.ዋ ማሳደግ ተችሏል፡፡

በዚህ ረገድ ከውሃ ሀይል የመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል የአንበሳውን ድርሻ የያዘ ሲሆን፤ 1 ሺህ 599 ሜ.ዋ በማመንጨት ወደ 9 ሺህ 50 ሜ.ዋ አድጓል፡፡

ከንፋስ እና ከፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚደረገው ጥረትም በተመሳሳይ ውጤት እያመጣ ይገኛል።

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአብነት ይጠቀሳል።

29 ተርባይኖች ያሉት የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 100 ሜጋዋት ያመነጫል።

እያንዳንዱ ተርባይን 3 ነጥብ 46 ሜጋዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ሲኖረው፣ የተርባይኖቹ ቁመት 84 ሜትር የሚደርስ እና የንፋስ ኃይል ማመንጫ የደረሰበትን የመጨረሻውን ቴክኖሎጂ የታጠቀ ነው።

የኢትዮጵያ እና የዴንማርክ መንግሥታት አጋርነታቸውን ያሳዩበት ፕሮጀክቱ፤ በኢትዮጵያ ተቋራጭ የተገነባ እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተቆጣጣሪነት የተሰራ መሆኑ ከንፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ የማመንጨት ሀገራዊ ትልምን ከፍ ያደርጋል።

በፀሐይ ኃይል ያለው የሶላር ኢነርጂ ልማት በተመሳሳይ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ላይ መገኘቱ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ያሳያል።

በሌላ በኩል በዘጠኝ ወራት አጠቃላይ የተመረተው የኤሌክትሪክ ኢነርጂ 27 ሺህ 401 ጊጋ ዋት ሰዓት ማምረት ተችሏል፡፡

የሀይል ማመንጫ ጣቢያዎች ዝግጁነት /Plant Availability/ 88 ነጥብ 2 በመቶ ሲሆን፤ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመር ዝርጋታ ከ141 ነጥብ 83 ሺህ ኪ/ሜ ወደ 148 ነጥብ 6 ሺህ ኪ/ሜ ደርሷል፡፡

ፍትሀዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት በማረጋገጥ በሀገሪቱ ያለውን የኃይል ፍላጎት የተሟላ ለማድረግ ውጤታማ ተግባር መከናወኑ በቀጣይ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ወሳኝ ነው።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሀገራት በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት ተሰሚነቷን ከማሳደግ በተጨማሪ ኢኮኖሚዋን ለመደገፍ የላቀ ሚና አለው።

ከኤሌክትሪክ ሀይል ሽያጭ የተገኘ ገቢ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። በዘጠኝ ወራት 24 ሺህ 940 ጊጋ ዋት ሰዓት በመሸጥ 365 ነጥብ 99 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱ የዘርፉ ተስፋ ከፍተኛ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን የታዳሽ ኃይል እምቅ አቅም በመጠቀም የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተሰሩ ስራዎች ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው፤ ኢኮኖሚውን እየደገፉ ነው።

ይህንን ተጨባጭ ተስፋ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግና አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ ሲሆን፤ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

Share this Post