ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሸጋገር በሚሰሩ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጨባጭ ውጤት እየመጣ ነው ተባለ።

ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሸጋገር በሚሰሩ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጨባጭ ውጤት እየመጣ ነው ተባለ።

ግንቦት 15/2018 ዓ.ም (ውኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት አካል የሆነው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀላባ ዞን የተገነባው የ1ኛ ጤፎ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የምረቃ ስነስርዓት ላይ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሸጋገር በሚሰሩ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጨባጭ ውጤት እየመጣ መሆኑ ተገለፀ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውሃ፣ መስኖና ማዕድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ኃይሉ ጥራት ያላቸው የመጠጥ ውሃ ተቋማትን በመገንባት የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግርን ለማቃለል በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የውሃን ችግር መቅረፍ የጤናን፣ የትምህርትን የግብርናንና ሌሎች ልማቶችንም ማስቀጠል በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የ1ኛ ጤፎ ቀበሌ ነዋሪ ሀጂ አብዱልራህማን ኢሰም እና ሀጂ ዱበላ ኢማም ኢብራሂም በበኩላቸው ነብሰጡር፣ አራስና ህፃናት ሴቶች ከሌሊቱ 10 ሰአት ጀምሮ በእግር ረጅም ርቀት ተጉዘው የሚያመጡት ውሃ ንፅህናው ያልተጠበቀ ከመሆኑም በላይ በመንገድ እየፈሰሰ የሚያልቅበት ጊዜም እንደነበር አስታውሰዋል።

ውሃን ለመጠጥም ሆነ ንፅህናን ለመጠበቂያ ከነልጆቻቸው ረጅም ርቀት ይጓዙ እንደነበር የገለፁት ሌላኛዋ የቀበሌው ነዋሪ ወ/ሮ ፈረጁ ሱሌማን በውሃ ፍለጋ ወቅት በመንገድ ላይ የሚወልዱ ሴቶችም እንደነበሩም በማስታወስ፤ አሁን በየቤታችን ንፁህ ውሃ በማግኘታችን መንግስታችንን እያመሰገንን፤ ቦኖዎቹን እንደ አይናችን ብሌን እንጠብቃለን ብለዋል።

የለቴንሳ አክሲዮን ማህበር የውሃ አማካሪና የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ተፈራ ማሞ በበኩላቸው ባርገሞ ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማህበር በተባለ ኮንትራክተር የተገነባና ለቴንሳ አክሲዮን ማህበር የቁጥጥር ስራውን ሲከታተል የነበረ ሲሆን የፍሎራይድ ማጣሪያ እንደተገጠመለትና በየሁለት አመቱ መፀዳት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ኢ/ር ተፈራ አክለውም በዲዛይኑ መሰረት 5ሺ ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ የታሰበ ቢሆንም አጎራባች ክልል ላይ ያሉ የቀበሌ ነዋሪዎችንም ጨምሮ ከ10ሺ በላይ ተጠቃሚ በማድረግ ጫና እንዳይበዛ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥ የቀበሌው ነዋሪ ፕሮጀክቱን መንከባከብ ይገባል ብለዋል።

ፕሮጀክቱን በባለቤትነት ያሰራው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሲሆን የክልሉ፣ የዞን የወረዳውና የአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፎም አለበት ብለዋል።

የ1ኛ ጤፎ ቀበሌ አስተዳደር አቶ ባሙድ መሀመድ በቀበሌው በቃላት የማይገለፅ የውሃ ችግር የነበረ በመሆኑ ልጆች ከሩቅ ቦታ የሚጠጣ ውሃ ለመቅዳት ትምህርታቸውን ያቋርጡ ነበር፤ አሁን ግን በየጊዜው ንፅህናቸውን እየጠበቁ የሚጠጡትም ውሃ ይዘው ወደ ትምህርት ቤት መሄድ በመቻላቸው የቀበሌው የውሃ ችግር ተቀርፏል ብለዋል።

ነዋሪዎቹ መንግስት ላደረገላቸው አስተዋፅኦ አመስግነው፤ በቀጣይም ቀሪ መሰረተ ልማቶች እንደሚሟላላቸው እምነታቸውን ገልፀዋል።

Share this Post