የግድቤን በደጄ የሦስት ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተካሄደ ነው።

የግድቤን በደጄ የሦስት ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተካሄደ ነው።

አዳማ፣ ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ ባዘጋጁት መድረክ የግድቤን በደጄ የሦስት ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ፍላጎት ሆቴል እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአስቸኳይ ጊዜና ልዩ ድጋፍ ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ ሠላማዊት ተወልደ እንደገለፁት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ንጹህ የመጠጥ ውሃን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ከገጸ- ምድርና ከከርሰ -ምድር የውሃ ሃብት በማቅረብ ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

አያይዘውም በሃገሪቱ ውሃ አጠርና ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲቻል በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በክቡር ዶ/ር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ አነሳሽነት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የግድቤን በደጄ ፕሮጀክት ተቋቁሞ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የዝናብ ውሃን ከጣራ ላይ በማሰባሰብ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተቻለ ነው ብለዋል።

በዕለቱ የተዘጋጀው መርሃ ግብር ዋና ዓላማም ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም ድረስ ባሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በዚሁ ፕሮጀክት የተሰሩ አፈጻጸሞችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመገምገም በተሳታፊዎቹ የሚነሱትን ሃሳብና አስተያየቶች በማካተት በቀጣይ በተሻለ ሁኔታ የሚተገበርበትን መንገድ ለመቀየስ እንዲቻል መሆኑንም ወ/ሮ ሠላማዊት ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳ/ር አቶ ታምሩ ፍቃዱ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ የግድቤን በደጄ ፕሮጀክት ቴክኖሎጂ በተጀመረበት ወቅት በዲዛይን ስራ፣በሰርቶ ማሳያ እና በማሻሻያ ስራዎች ተሳትፎ እንደነበረው አስታውሰው ወደ ትግበራ ከተገባ በኋላም ድጋፍና ክትትል እያካሄደና የአቅም ግንባታ ስራ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚሁ ፕሮጀክት በሃገሪቱ የውሃ ሽፋን በማዳረስ በኩልም ውሃ ያልተዳረሰባቸው አካባቢዎች መኖራቸውንና በተለይም እምብዛም ግልጋሎት ላይ ያላዋልነውን የዝናብ ውሃ በማሰባሰብ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ አዋጭ፣ ተደራሽና ቀላል በሆነ ቴክኖሎጂ እንዲተገበር የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አቶ ታምሩ ተናግረዋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአስቸኳይ ጊዜና ልዩ ድጋፍ ዴስክ ኃይድሮጂኦሎጂስት አቶ አበራ ኩምሳ የግድቤን በደጄ ፕሮጀክት የሦስት ዓመት የስራ ክንውን፣ በሂደት ከነበሩ ትግበራዎች የተወሰዱ ልምዶችና ተሞክሮዎች እንዲሁም የቀጣይ ጊዜ የስራ አቅጣጫዎችን የሚመለከት የአፈጻጸም ሪፓርት አቅርበዋል።

አቶ አበራ በገለፃቸው ፕሮጀክቱ በሃገሪቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በሲዳማ እና በኦሮሚያ ክልሎች እንደሚተገበርና እነዚህ ክልሎች የተመረጡበት ዓብይ ምክንያትም ድርቅ የተስፋፋባቸውና ውሃ አጠር በመሆናቸው ምክንያት በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ታሳቢ በማድረግ መሆኑንም አመላክተዋል።

በተለይም በትምህርትና በጤና ተቋማት ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን የተደረገ ሲሆን ወደ ትግበራ ከተገባ በኋላ የተማሪ መጠነ ማቋረጥንና እናቶች በወሊድ ወቅት የሚያጋጥሟቸውን የጤና ችግሮች በመቅረፍ ረገድ ፕሮጀክቱ ለማህበረሰቡ የጎላ ጠቀሜታ ማስገኘቱንም አቶ አበራ አስረድተው ከቀረበው ሪፖርት በመነሳት ከተሳታፊዎቹ ለተነሱ ሃሳብና አስተያየቶች ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በመቀጠል ክልሎቹ የአፈጻጸም ሪፖርት እያቀረቡ ሲሆን በትግበራ ወቅት ባጋጠሙ ችግሮችና በመፍትሄዎች ዙሪያ እየመከሩ ነው።

መርሃ ግብሩ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በነገው ውሎም የወረዳዎች ተወካዮች የፕሮጀክቱን አፈጻጸም ሪፓርት የሚያቀርቡ ሲሆን በሚሰነዘሩ ሃሳቦችና አስተያየቶች የቀጣይ ተግባራት የማሻሻያ ግብዓቶች የሚሰበሰቡ ይሆናል።

በመድረኩ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዴስክ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተርና አስተባባሪዎች እንዲሁም የክልሎችና የወረዳ ተወካዮች እየተሳተፉበት ነው።

Share this Post