የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና በጀት በማጠናቀቅ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እናረጋግጣለን።
የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና በጀት በማጠናቀቅ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እናረጋግጣለን።
ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር
ሀላባ፣ ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት አካል የሆነውና ከ126 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የ1ኛ ጤፎ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
በመርሃግብሩ ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ወክለው በመድረኩ መልክት ያስተላለፉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታምሩ ገደፋ ተቋሙ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽንን ዘርፍ ለማሻሻል የ10 ዓመታት መሪ ዕቅድ በመንደፍ በተለያዩ ክልሎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሆኗል ብለዋል።
ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በድርቅ የሚጠቁና በረሃማ አካባቢዎች ላይ የሚተገበር ፕሮጀክት በመሆኑ፤ የ1ኛ ጤፎ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የፍሎራይድ ማጣሪያ የተገጠመለትና በእናቶችና ህፃናት ላይ ይደርስ የነበረውን የጤና እክል የሚያስቀር ነው ያሉት አቶ ታምሩ 9 ኪሎ ሜትር የቧንቧ ዝርጋታ፣ 9 የመጠጥ ውሃ ቦኖዎችና 7 የእንስሳት ማጠጫ ገንዳዎችን ያካተተ ግንባታ ስለሆነ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥ የክልል፣ የዞን፣ የወረዳና የአካባቢው ማህበረሰብ ተንከባክቦ እንዲያስቀጥል አሳስበዋል።
አቶ ታምሩ አያይዘውም ፕሮጀክቱ ልዩ ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ አስፈላጊውን የአገልግሎት ክፍያ በመፈፀም ዘላቂ እንዲሆን ለማድረግ ለአካባቢው ነዎሪዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ ይገባልም ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስም አመስግነዋል።
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑርዬ በበኩላቸው ውሃ የሚያልቅ ሀብት በመሆኑ፤ ሀላባ ላይ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ሳይሆን ውሃ ብቻ የረጅም ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰው፤ ፕሮጀክቱ የሁልጊዜ ክትትል የሚፈልግ ስለሆነ ለረጅም አመታት እንዲያገለግል ህብረተሰቡ በትኩረት እንዲጠብቀው አደራ ብለዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀላባ ዞን አቶቲ ኡሎ ወረዳ 1ኛ ጤፎ ቀበሌ የተገነባውና ከ10 ሺህ በላይ የአካባቢውን ማህበረሰብንና አጎራባች ቀበሌዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የጤፎ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የምረቃት ስነስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን ሁሴን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የተቸረች ቢሆንም የተፈጥሮን በረከት በፍትሃዊነት በመጠቀም ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
ውሃ በሌለበት ልማት አይታሰብም ያሉት አቶ ሙህዲን የውሃ እጥረት ለዜጎች ዕድገት እንቅፋት እንዳይሆን የሁሉም ቅንጅት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ለፕሮጀክቱ ዕውን መሆን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ አስተዋፅኦ ያበረከቱትን አካላት ሁሉ አመስግነዋል።
በመርሀ ግብሩ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።