የተቀናጀ አስተዳደር የውሃ ሀብትን ለቀጣይ ትውልድ ጠብቆ ለማስተላለፍ

የተቀናጀ አስተዳደር የውሃ ሀብትን ለቀጣይ ትውልድ ጠብቆ ለማስተላለፍ

ግንቦት/14/2018 ዓ.ም (ዉ.ኢ.ሚ) ውሃ የሰዎች የዕለት ተዕለት የህልውና መሠረት ብቻ ሳይሆን የሀገራት የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ማህበራዊ መረጋጋት እና የፖለቲካ ትስስር ማጠናከሪያ ዋና ግብዓት ነው።

በአየር ንብረት ለውጥ እና በሕዝብ ቁጥር መጨመር ምክንያት የውሃ ዋስትና ዓለም አቀፋዊ ስጋት በሆነበት በዚህ ወቅት ይህንን ውድ የተፈጥሮ ሀብት በተለመደው መንገድ ማስተዳደር የብክነት ተጋላጭነትን ከፍ ያደርጋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና እና የዘላቂ ልማት ጉዞ እውን ለማድረግ ትኩረት ከሰጠቻቸው ጉዳዮች መካከል የውሃ ሀብትን በተቀናጀ መንገድ ማስተዳደር አንዱ ጉዳይ ሆኗል።

ሀገሪቱ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደርን (IWRM) ይበልጥ ማጠናከር በምትችልባቸው ስልታዊ አቅጣጫዎች ላይ በዕቅድ በመመራት አመርቂ ውጤት እያመጣች ነው።

የውሃና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን በተቀናጀ መልክ ለማልማት ሀገሪቱ ያሏትን ተፋሰሶች መሰረት ባደረገ መልኩ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚያስፈልገው የውሃ አለኝታ እንዲኖር ለማድረግ የውሃ አካላትን ደህንነት ለመጠበቅ በማቀድ እየተሰራ ነው።

በዚህም የውሃ ሀብት አስተዳደር አካል የሆነውን አጠቃላይ መረጃ የማደራጀትና ተፋሰስን ማዕከል ያደረገ የተፋሰስ ዕቅድ በማዘጋጀት አግባብነት ያላቸው አካላት በሙሉ የሚሳተፉበትን ማዕቀፍ ተፈጥሯል።

ውሃ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ መሆኑን በመረዳት የተቀናጀ የውኃ ሃብት አስተዳደርን ማጠናከር የሚያስችሉ ወሳኝ ርምጃዎች ተወስደዋል። ውሃ የህልውናችንና የኢኮኖሚያችን መሰረት እንዲሁም ለሀገራዊ ብልጽግና፣ ሰላም እና ልማት ወሳኝ የሆነ ስትራቴጂካዊ ሀብት መሆኑን ከግምት ያስገባ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።

ውድ የሆነውን የውሃ ሀብት ለማስተዳደር፣ ደህንነቱን ለመጠበቅ፣ ለመምራትና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በትብብር መስራት አስፈላጊ በመሆኑም የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

ዜጎች ደህንነቱ የተጠበቀ ውሃ ማግኘት እንዲችሉ ወንዞች፣ ሐይቆች እና እርጥበታማ መሬቶች ሁሉ ደህንነታቸው ተጠብቆ ዘላቂነት ያለውን አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ሀብቱን ጠብቆ በማቆየት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ መንከባከብ እና በጥበብ መምራት ያስፈልጋል።

እንደሀገር የውሃ ሃብት ልማት እና አስተዳደርን በማጠናከር ረገድ አስደናቂ እድገት እየታየ ሲሆን፤ በተፋሰስ ልማት አስተዳደር፣ በኃይድሮሜትሮሎጂ የመረጃ ስርዓትና በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም መርሐ ግብሮች ላይ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው።

የውሃ፣ የኢነርጂ፣ የአካባቢና የስነምህዳር፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር አቀራረቦችን ማጠናከር ተገቢ በመሆኑ በስፋት ተሰርቶ ውጤት መጥቷል።

የሚመለከታቸውን ባለድርሻዎች በማቀናጀት ሀገሪቱ ያላትን የውሃ ሀብት በመለየት ጥቅም ላይ እንዲውል ከማድረግ ጀምሮ በየደረጃው የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸው የሚፈለገውን ውጤት በማምጣት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ ሀብቶቻችንን በጋራ የማልማትና የመጠቀም ሂደት አስፈላጊነትና በልዩ ልዩ የውሃ ተጠቃሚዎች መካከል አጠቃቀም ላይ መግባባት ወሳኝ በመሆኑ የውሃ ሃብት አጠቃቀም በአግባቡ እንዲመራ የዘርፉ ተዋናዮች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው።

የውሃ ጥራትን በማስጠበቅ፣ መጠኑን በማወቅና በውሃ ምደባ አሰራር ተደራሽ በማድረግ እንዲሁም የወንዝ ዳርቻን በማስጠበቅ፣ የእንቦጭ አረም መስፋፋትን በመቆጣጠር በተፋሰሶች ላይ ያሉ ችግሮችን መፍታት የተቀናጀ አሰራርን ስለሚጠይቅ መግባባት እና መናበብ ያስፈልጋል።

የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ወጥነት ባለው አግባብ መተግበርን ይጠይቃል።

Share this Post