ፕሮጀክቱ የውሃ ሀብታችን ለብልፅግናችን የሚለውን መርህ የሚያረጋግጥ ነው። /ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ

ፕሮጀክቱ የውሃ ሀብታችን ለብልፅግናችን የሚለውን መርህ የሚያረጋግጥ ነው።

------------------------------------------------------

ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ

ዓለም ገበያ፣ ግንቦት 13/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በCR-WASH የሳንኩራ ባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ሳንኩራ ወረዳ ጀጀብቾ ለምለም ቀበሌ በ430 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነባው የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

በፕሮጀክቱ ምርቃት ላይ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለዜጎች ንፁህ የመጠጥ ውሃና የሳኒቴሽን አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የሰራው ፕሮጀክት የውሃ ሀብታችን ለብልፅግናች የሚለውን መርህ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ክቡር አምባሳደር አክለውም የውሃ ሀብትን በተገቢው መንገድ ማስተዳደርና ለዘላቂ ልማት ለማዋልና ከሚሰሩ በርካታ ስራዎች መካከልም ለሳኒቴሽን ዘርፉም ልዩ ትኩረት ስለሚያስፈልግ ፕሮጀክቱን አጠናቀን ለህብረተሰቡ ስናስረክብ፤ መንከባከብ ብቻ ሳይሆን ብክነትንና ብክለት በመቀነስ፣ ውሃውን በቁጠባ መጠቀምና የውሃ አገልግሎት ተቋም በሚዘረጋው የክፍያ ስርዓት ክፍያቸውን በወቅቱ እንዲከፍሉም አሳስበዋል።

ንፁህ የመጠጥ ውሃ ህይወትን ለማስቀጠል አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ውስጥ ተጠቃሽ ነው ያሉት ክቡር አምባሳደር ውሃ ባለበት ቦታ ሁሉ ህይወት እንዲቀጥል ምክንያት ስለሆነም፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የውሃ ሀብትን ማስተዳደር የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።

ለፕሮጀክቱ ስኬት ከፍተኛ በጀት የተመደበ ሲሆን ለህብረተሰቡ ጤና፣ ለሴቶችና ለህፃናት፣ ለትምህርት ብሎም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናን ለማቅለል የላቀ ሚና እንዳለውም አክለዋል።

ፕሮጀክቱን በይፋ ያስጀመሩት የማዕከላዊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው የቤተሰብና የማህበረሰብ ብልፅግና ማረጋገጥ የመንግስት ብልፅግና ዓብይ አጀንዳዎች ሲሆኑ፤ ውሃ ለማህበረሰቡ የሚሰጠው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በለውጡ መንግስት በተለያየ ጊዜ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና የህዝብ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው በመሆኑ የተመረቁ ፕሮጀክቶችን ህዝቡ በአግባቡ እንዲጠብቅና እንዲያስተዳድር ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

ክቡር ዶ/ር እንዳሻው አክለውም ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የሳንኩራ ባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት 69,825 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከ20 አመታት በላይ ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል፣ በ13 ቀበሌዎች ላይ 42 የውሃ ቦኖዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚችልና ዘመናዊ የመፀዳጃ ቤቶችን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።

በመርሀ ግብሩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ሸርሞሎ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ፣ በውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪና የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተወካይ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክላስተር አስተባባሪዎች፣ የክልል እና የስልጤ ዞን አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

Share this Post