የብሔራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም የሶስተኛው ሩብ ዓመት የአፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ።

የብሔራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም የሶስተኛው ሩብ ዓመት የአፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ።

ሀዋሳ፣ ግንቦት 13/2018 ዓ.ም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በብሔራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም ሲከናወኑ የቆዩ ተግባራትን እና የ2018 ዓ.ም የሶስተኛው ሩብ ዓመት አፈጻጸምን ከባለድርሻ አካላት ጋር በሀዋሳ እየገመገመ ነው።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ታምሩ ደገፉ ፣ ፕሮጀክቶች በመጀመሪያና በመጨረሻ ደረጃ ላይ ፈተና እንደሚያጋጥማቸው ጠቅሰው፣ የተጀመሩ ስራዎችን በቀሪው አጭር ጊዜ በውጤታማነት ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አቶ ታምሩ ፕሮግራሙ ከ6 ዓመታት በላይ ሲተገበር በተከታታይ ግምገማ እየተመራ መሆኑን ገልጸው፣ በመጠጥ ውሃ ዘርፍ በገጠር 94 በመቶ እና በከተማ 69 በመቶ ተደራሽነት መመዝገቡን አስታውቀዋል። በሳኒቴሽን ዘርፍም 80 በመቶ እንዲሁም በአጠቃላይ 75 በመቶ ተደራሽነትን ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

እንዲሁም ለ2019 ዓ.ም እቅድ ክልሎች በየክልላቸው ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት የፕሮጀክቶች ቀጣይነት ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የዋን ዋሽ ፕሮግራም የምዕራፍ ሶስት አተገባበር ከቀደሙት በተለየ መልኩ እንደሚተገበር የገለጹት አቶ ታምሩ፣ ለፕሮግራሙ ቀጣይ ስኬት 103 ወረዳዎችና 18 ከተሞች እንደመነሻ መለየታቸውን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የሲዳማ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ም/ሀላፊ አቶ ሀይለየሱስ ኤሊያስ ፣ መድረኩ በዋን ዋሽ ፕሮግራም ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ስራዎችን በጥልቀት የሚገመገም አስፈላጊ መድረክ መሆኑን ገልጸው፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በውይይቱ ላይ የውሃ ዘርፍ የ3ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት፣ የግዢ ሂደት፣ የጤናና የትምህርት ዘርፎች የ3ኛ ሩብ ዓመት እና የድምር አፈጻጸም ሪፖርቶች፣ የፋይናንስ ስርጭትና አጠቃቀም፣ የ2019 ዓ.ም ረቂቅ በጀት እንዲሁም የምዕራፍ ሶስት የዋን ዋሽ ፕሮግራም አተገባበር ላይ የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሁፎች ለውይይት ቀርበዋል።

የውይይቱ ዋና ዓላማ እስካሁን የተመዘገቡ ውጤቶችን በመገምገም የምዕራፍ ሶስት የዋን ዋሽ ፕሮግራምን በተሻለ አፈጻጸም ለማስፈጸም የሚያስችል ግንዛቤ መፍጠር መሆኑ ተጠቁሟል።

በመድረኩ ከውሃና ኢነርጂ፣ ከጤና፣ ከትምህርትና ከፋይናንስ ሚኒስቴሮች እንዲሁም ከክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮዎች ኃላፊዎችና የዘርፉ ሙያተኞች እየተሳተፉ ነው።

Share this Post