የዜጎችን ኑሮ እያሻሻለ የሚገኘው የኃይል አቅርቦት
የዜጎችን ኑሮ እያሻሻለ የሚገኘው የኃይል አቅርቦት
ግንቦት/13/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ሀገር ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥና የዜጎቿን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ከሚያስፈልጓት መሠረታዊ ምሰሶዎች መካከል አስተማማኝና ተደራሽ የኃይል አቅርቦት በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የኢንዱስትሪ፣ የዲጂታልና የገጠር ሽግግርን ዕውን ለማድረግ በምታደርገው ጥረት የኤሌክትሪክ ኃይል ልማትና አስተዳደር ዘርፍ የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
በዚህም የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ሀገሪቱ ያላትን ዕምቅ የታዳሽ የኃይል አቅም ወደ ውጤት በመቀየር በስፋት እየተሰራ ነው። በተለይም የውሃ፣ የንፋስና የፀሐይ ብርሃንን በመጠቀም ኃይል ማመንጨት አቅምን ለማሳደግ፣ ፍትሐዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሰራሮችን ለመተግበር ዘርፈ-ብዙ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑ ይገኛል።
ህብረተሰቡን በኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ (ግሪድ) ጋር የተገናኙ እና ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ ውጪ በሆነ የኃይል አማራጭ (ኦፍ ግሪድ) የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ በሚደረገው ጥረት ውጤት እየተመዘገበ ነው።
በዚህም በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ዘጠኝ ወራት ብቻ 103 አዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል።
ፍትሐዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተከናወነው ዘርፈ-ብዙ ተግባር ከጤና እና ማኅበራዊ ተቋማት በተጨማሪ በእነዚህ አዳዲስ አካባቢዎች የሚገኙ ከ31 ሺህ በላይ ቤተሰቦች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል ተፈጥሯል።
ኃይል ከማግኘት አኳያ ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ (ግሪድ) ጋር ከተገናኙት ባሻገር የገጠር ከተሞችና መንደሮች በፀሐይ ኃይል አማራጭ (ኦፍ ግሪድ) የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል። ይህም መንግሥት ከዋናው ግሪድ ርቀው ለሚገኙ አካባቢዎች የሰጠውን ትኩረት ያሳያል።
በተጨማሪም ተደራሽነትን ከማስፋፋት አንጻር ባለፉት ዘጠኝ ወራት 423 ሺህ 200 አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን፤ አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ18 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ አለው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 5 ነጥብ 64 ሚሊዮን የደረሰውን አጠቃላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር ለማሳደግ እና ተደራሽነትን ለማስፋፋት የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከብሔራዊ ግሪድ የራቁ የገጠር አካባቢዎችን በአማራጭ ታዳሽ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የማድረግ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል። በዚህ ረገድ በክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ በጀት ወጪ ተደርጎባቸው የተገነቡ የሶላር ሚኒግሪድ የኃይል ማመንጫዎች ተጠናቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው።
መንግሥት በሀገራዊ ለውጡ የተፈጠሩ ዕድሎችንና ፀጋዎችን በመጠቀም በከተማም ሆነ በገጠር የህዝብን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የቻሉ የልማትና የሁለንተናዊ ብልጽግና ትልም ስኬት መሠረት የጣሉ ስኬቶች መመዝገባቸውን ቀጥለዋል።
የአርሶና የአርብቶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ ተጠቃሚነቱን ከማረጋገጥ ባሻገር በገጠሩ ህብረተሰብ ህይወት ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት የገጠር ሽግግርን ዕውን ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል።
ለተያዘው የሁለንተናዊ ብልጽግና ጉዞ የገጠር ሽግግርን ዕውን ማድረግ መሰረታዊ ጉዳይ ሲሆን፤ የገጠሩ ህብረተሰብ በአማራጭ የታዳሽ ኃይል አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል።
የተገነቡ እና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ የሶላር ሚኒግሪድ ኃይል ማመንጫዎች ከፍተኛ ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው በመሆኑ ከመብራት አገልግሎት ባለፈ ለተቀናጀ ልማትና ዕድገት የጎላ አስትዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው።
የሶላር ሚኒግሪድ ኃይል ማመንጫዎች ለሚቀጥሉት 20 እና 30 ዓመታት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት መስጠት እንዲችሉ ተደርገው በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ በመሆናቸው ህብረተሰቡ መሰረተ ልማቶቹን በአግባቡ መያዝ ይጠበቅበታል።
በብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር የራቁ አካባቢዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተተገበረ የሚገኘው የአደሌ ፕሮጀክት በርካታ አካባቢዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መጀመሩ በህብረተሰቡ ኑሮ ላይ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል።
በ2022 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ አካባቢዎችን 75 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን፤ በኦፍ ግሪድ ቴክኖሎጂ በተለይም በፀሐይ ኃይል ልማት ዘርፍ ከ26 በመቶ በላይ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስኬትን ጨምሮ በአጠቃላይ የዜጎች ኑሮ መሻሻል በቀጣይ ዓመታት 9 ሚሊየን ቤተሰቦችን የኤሌትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በብሔራዊ ኤሌትክሪፊኬሽን ፕሮግራም ከ2 ሚሊየን በላይ ቤተሰቦች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ተደርጓል።
ከብሔራዊ ግሪድና ከግሪድ ውጪ በቀጣይ ዓመታት ለ9 ሚሊዮን ቤተሰቦች የኤሌክትሪክ ሀይል ለማቅረብ ስልት ተነድፎ እየተሰራ ሲሆን፤ ከብሔራዊ ግሪድ ርቀው የሚገኙ አካባቢዎችም በቤተሰብ እና በማህበረሰብ ደረጃ የሶላር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ተደራሽ የማድረግ ግብ ተቀምጧል።
ይህንን ግብ ለማሳካት መንግሥት ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በመተባበር እየሰራ ይገኛል።