የከተማ የውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረገ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑ ተገለጸ። ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ
አዋሳ# ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በ2 ቢሊየን ብር ወጪ ዘመናዊ የፈሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።
ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ እንዳሉት፥ በኢትዮጵያ ፈጣን የከተማ እድገት በነባሩ የሳኒቴሽን መሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።
የከተሞች በፍጥነት መስፋፋት ለሚሊዮኖች የተገቢ የፍሳሽ ቆሻሻ አያያዝ አገልግሎት አለመኖር ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ችግሩን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
መንግስት የከተማ ሳኒቴሽንን ሀገራዊ ቅድሚያ አድርጎ በመሠረተ ልማት ኢንቨስት ማድረግ፣ ተቋማትን ማጠናከር እና ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የሳኒቴሽን ክፍተቱን ለመሙላት እየተሰራ ነውም ብለዋል።
ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ሁለተኛውን የከተማ የውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት (UWSSP-2) በ774.387 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት እየተተገበረ መሆኑን አንስተው፤ በአጠቃላይ 3.742 ሚሊዮን ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
በፕሮጀክቱ የሳኒቴሽን አገልግሎት እንደሚሻሻል፣ ዜጎች በተሻሻለ የውሃ አቅርቦትና የአሠራር ብቃት እንሚጠቀሙም አብራርተዋል።
እስካሁን 837,675 ሰዎች ደህንነቱ የተጠበቀ የሳኒቴሽን አገልግሎት ሲያገኙ፣ 915,846 ሰዎች ደግሞ በከተማ አካባቢ የተሻሻለ የውሃ ምንጭ አግኝተዋል ሲሉም ገልጸዋል።
ዛሬ ግንባታው የጀመረው የሐዋሳ የፍሳሽ ቆሻሻ እና ሴፔጅ ማጣሪያ ፕላንት (FSTP) ለሐዋሳ ከተማ የወደፊት የሳኒቴሽን አገልግሎት ታላቅ ኢንቨስትመንት እንደሆነም ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከCGCOC GROUP Co., LTD የስራ ተቋራጭ ጋር እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 02 ቀን 2025 ውል የተፈረመ ሲሆን 262,753,655.91 ብር እና 11,154,205.76 የአሜሪካ ዶላር ዋጋ የሚከናወን ይሆናል በማለት አብራርተዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ÷ በከተሞች ያለውን የፈሳሽ እና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ለማዘመን በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የለውጡ መንግሥት ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ግንባታን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና ጥራት በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ እያጠናቀቀ እንደሚኝ አብራርተዋል፡፡