በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ወደ ተግባር የገባው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ እና አይቲ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ከፍተኛ ስኬት እያስመዘገበ ይገኛል።

ታዳሽ ኃይል የአምራች ኢንዱስትሪው የዕድገት መሰረት በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ወደ ተግባር የገባው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ እና አይቲ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ከፍተኛ ስኬት እያስመዘገበ ይገኛል። ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የሚፈለገውን ውጤት ያመጣ ዘንድ ባለድርሻዎች በመቀናጀት እና በመናበብ መስራታቸው ወሳኝነት አለው። በዚህ ረገድ መንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ እና ሌሎች ተዋናዮች ተቀራርበው መስራት የሚችሉበት መደላድል ተፈጥሯል። ለአብነትም አምራች ኢንዱስትሪው ከሚያስፈልጉት ወሳኝ ግብዓቶች መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል በመሆኑ የኃይል አቅርቦት ላይ የሚሰራው ዘርፍ ሚናውን በአግባቡ እየተወጣ ነው። አረንጓዴ ኢኮኖሚን የመገንባት ዓላማን በመያዝ ሀገራዊ ብልጽግናን ዕውን ለማድረግ የምትተጋው ኢትዮጵያ ያላትን የታዳሽ ኃይል ጸጋ በስፋት እያለማች ትገኛለች። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኃይል ማዕከል የማድረግ ራዕይ በመሰነቅ የሃይድሮ፣ የነፋስ፣ የሶላር እና የጂኦተርማል ኃይል የሚያመነጩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቅተዋል፤ ኮይሻን ጨምሮ በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችም ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የነበሩበትን በርካታ ውስብስብ ችግሮች በመፍታት ለብርሃን እንዲበቃ በማድረግ ረገድ የለውጡ መንግሥት የአመራር ቁርጠኝነቱን አሳይቷል። አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችም እንደ ጀርባ አጥንት ሆኖ በማገልገል ላይ ሲሆን፤ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ "የመደመር" ፍልስፍና ውጤት አንዱ ዘርፍ ለሌላው የህልውና መሰረት የሚሆንበትን ሁኔታ ፈጥሯል። መንግሥት ሀገራዊ የኃይል አቅርቦትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ግልጽ ዕቅዶችን አስቀምጦ ሰርቷል፤ እየሰራም ይገኛል። ይህ ቁርጠኝነት በውሃ፣ በፀሐይ፣ በነፋስ እና በጂኦተርማል ኃይል ማመንጫዎች ላይ በስፋት ኢንቨስት በማድረግ አስተማማኝ የኃይል አማራጮች ጥቅም ላይ እንዲውሉ አስችሏል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል እንድትሆን በንጹህና ታዳሽ ኃይል ላይ እየተሰራ እንደሚገኝና በበቂ ደረጃ ኃይል ማምረት ለኢንዱስትሪ ወሳኝ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል። በዚህም የታዳሽ ኃይል ምንጮችን ማስፋፋት ላይ በትኩረት በመስራት ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ወደ ኃይል በመቀየር የተሳካ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ጉዞ ውስጥ ነች። እያደገ ከሚገኘው የኢንዱስትሪ ዘርፍና ተያይዞ ከሚመጣው የኃይል ፍላጎት ጋር የሚመጣጠን የታዳሽ ኃይል አቅም ለመገንባት የኃይል ምንጮችን ለማብዛት ተሰርቷል። በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሰፊ ቦታ የሚይዘውን የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ዘርፍ ለማሳደግ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ መግባት ከፍተኛ አቅም ፈጥሯል። ከኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ባሻገር በሚገኙ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት በማድረግም በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃውን የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ጨምሮ በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በፀሐይ ኃይል ማመንጫ ዘርፍ ደግሞ አብዛኛውን ወራት የፀሐይ ብርሃን የምታገኘው ኢትዮጵያ÷ ይህንን የተፈጥሮ ጸጋ ለመጠቀም በርካታ ሥራዎችን በማከናወን የአምራች ኢንዱስትሪውን የኃይል ፍላጎት ለማርካት አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። በበቂ ደረጃ ኃይል ማምረት ካልተቻለ አምራች ኢንዱስትሪውን ውጤታማ ማድረግ የማይቻል መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ስራ ተሰርቷል። አሁን ባለው ተፈላጊነት የሚመረተው ታዳሽ ኃይል በዚህ ዓመት 23 በመቶ ላደገው የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች የኃይል ፍላጎት ምላሽ ሰጥቷል። ክቡር የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ኢትዮጵያ ከምን ጊዜውም በተሻለ ሁኔታ በርካታ ስራዎች እየሰራች መሆኑን ያነሳሉ። ከለውጡ ወዲህ የሀገሪቱ የኃይል አቅርቦት ከእጥፍ በላይ ማደጉን በመግለጽ፤ ቀደም ሲል ከ4 ሺህ ሜጋ ዋት ያልበለጠው የሀገሪቱ የኃይል ማመንጨት አቅም አሁን ላይ ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት እየተጠጋ ይገኛል ሲሉ ይገልጻሉ። ይህ ስኬት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዕድገት የላቀ አስተዋጽኦ በማድረጉ ምርታማነት ከመጨመር እና ሰፊ የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር፤ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር የድርሻውን እየተወጣ ነው። በመሆኑም መንግሥት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ዘርፉን ይበልጥ ለማጠናከርና የጀመራቸውን አበረታች ሥራዎች ለማስቀጠል ግልጽ ዕቅዶችን አስቀምጧል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም

Share this Post