አረንጓዴ ዐሻራ ለዘላቂ የውሃ ሃብት ልማት ጥበቃ ቀዳሚ መፍትሔ!
ግንቦት 6፣ 2018 (ው.ኢ.ሚ) ዓለማችንን በአሁኑ ወቅት እየፈተኑ ከሚገኙ ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸው ጫናዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትላቸው ቀውሶች በእጅጉ ከሚፈተኑት የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል ውሃ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።
በድርቅም ሆነ በጎርፍ እንዲሁም የገጸ ምድር ውሃ በደለል መሞላት በዘላቂነት የውሃ ልማትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ያደናቅፋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ውሃን ጨምሮ ለተፈጥሮ ሃብት የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ምላሽ ለመስጠት ተግባራዊ ርምጃ በመውሰድ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።
ከእነዚህ ተግባራት መካከል ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ሲሆን፤ በመርሐ ግብሩ ስኬት ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ስሟ በጉልህ እንዲጠቀስ አድርጓል።
በመንግሥት ቆራጥነት እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የኢትዮጵያውያንን ልብና ጉልበት በአንድነት ያስተሳሰረ ታላቅ ሀገራዊ ተግባር ሆኖ ቀጥሏል።
ይህ በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በይፋ የተጀመረው መርሐ ግብር ዛፍ ከመትከል ባሻገር ውሃን ጨምሮ ለተፈጥሮ ሀብቶቻችን ዋስትና የሰጠ ውጤት አስመዝግቧል።
መንግሥት ለመርሐ ግብሩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በባለቤትነት በመምራትና ህዝቡም ጥሪውን ተቀብሎ በነቂስ በመውጣት ላለፉት ዓመታት ያሳዩት ቁርጠኝነት የሀገሪቱን ደን ሽፋን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ብቻ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። ከዚህ ውስጥ 18 ነጥብ 7 ቢሊየኑ በዓባይ ተፋሰስ ላይ ብቻ የተተከለ ነው።
ይህም 40 በመቶ ድርሻ እንዳለው ያሳያል፥ ሆኖም ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ ውሃውን መጠቀም ብቻ ሳይሆን የመንከባከብ ስራም እየሠራች ማለት ያስችላል።
በዚህም የሀገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 23 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ ይህም ከቁጥር ባለፈ በተጨባጭ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለመጣው ለውጥ ማሳያ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በየዓመቱ ይወድም የነበረው 72 ሺህ ሄክታር ደን ወደ 3 ሺህ ሄክታር ዝቅ እንዲል ተደርጓል።
በወንዞች ላይ የሚፈጠረው ደለል እንዲቀንስ እና በወንዞች ላይ ይከማች የነበረው 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ቶን ዓመታዊ የደለል ክምችት ወደ 208 ሚሊየን ቶን እንዲቀንስ በማድረግ ለውሃ ሀብት ጥበቃ ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከተ ይገኛል።
በተመሳሳይ መልኩ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ይደርስ የነበረው 130 ቶን ዓመታዊ የአፈር መሸርሸር አሁን ላይ ወደ 54 ቶን ዝቅ እንዲል በማስቻል ለምርታማነት እና ለአፈር ለምነት ትልቅ በረከት ሆኗል።
መርሐ ግብሩ ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት መፋጠን አስተዋጽኦ እያበረከተ ሲሆን፤ ለወጣቶችና ለሴቶች የገቢ ምንጭ በመሆን ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ዜጎች የአረንጓዴ ስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ችግኞችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ በቤተሰብ ደረጃ ተጨማሪ ገቢና የምግብ ምንጭ መሆን ችሏል።
አረንጓዴ ዐሻራ ከላይ ከተጠቀሱት ጥቅሞች በተጨማሪ ለዘላቂ የውሃ ሀብት ጥበቃ በርካታ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ማየት ይቻላል።
ደን ማልማት የዝናብ ውሃ ወደ መሬት ውስጥ እንዲሰርግ በማድረግ የውሃ ምንጮችን ያጠናክራል፣ የአፈር መሸርሸርን ይቀንሳል፣ የዛፍ ሥር አፈርን በማቆየት ወደ ውሃ አካላት የሚደርሰውን ደለል ይቀንሳል።
ይህም የውሃ ጥራት ይጠብቃል፣ የጎርፍ አደጋ ይቀንሳል።
ደን ድንገተኛ ጎርፍን ስለሚቀንስ የውሃ አካላት በዘላቂነት ያገለግላሉ፤ ዝናብን በማመጣጠን የውሃ ሀብት ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ያግዛል።
በተጨማሪም የውሃ ትነትን በመቀነስ የውሃ ኪሳራ ያስቀራል።
ዘርፈ ብዙ ዓላማ በመያዝ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያውያን እና በመንግሥት ቁርጠኛ አመራር እየተተገበረ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ግቡን እያሳካ እዚህ ደርሷል።
በቀጣይም ይበልጥ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገና የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ በከፍተኛ ደረጃ እየደገፈ ተጠናክሮ ይቀጥላል።