የአሳይታና አፋምቦ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኑ።

የአሳይታና አፋምቦ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኑ። ሰመራ፣ ሚያዚያ 14/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) – የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአፋር ክልል አሳይታና አፋምቦ ወረዳዎች ከ596 ሚሊየን ብር በላይ በመዋል ያስገነባቸው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መዘጋጀታቸው ተገለጸ። ፕሮጀክቶቹ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ ባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ ስርዓቶች ሲሆኑ፣ ከ52,800 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተገልጿል። በሁለቱ ወረዳዎች ያሉ 8 ቀበሌዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሲሆን፣ 3 ታላላቅ ሪዘርቬሮችና 72 ኪሎ ሜትር የቧንቧ መስመር ዝርጋታ ያካተቱ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ፣ ፕሮጀክቶቹ የትምህርትና የጤና ተቋማትን ጨምሮ ለእንስሳት የሚያገለግሉ የውሃ መጠጫ ገንዳዎችን በመገንባት የህብረተሰቡን ስፋ ያለ የውሃ ፍላጎት ማሟላት አስችለዋል። ፕሮጀክቶቹ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ከማሻሻል ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማስገኘት የአካባቢውን የብልጽግና ጉዞ የሚደግፉ አስፈላጊ ኢንቨስትመንቶች መሆናቸው ተጠቅሟል። በፕሮጀክቶቹ የምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ የአፋር ክልል ር/መስተዳድር ክቡር አቶ አወል አርባ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልሉ አመራሮች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

Share this Post