በብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም በተዘጋጀው ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ የውይይት መድረክ ተካሄደ።
ሚያዝያ 08/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም በተዘጋጀው ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በካፒታል ሆቴል የውይይት መድረክ ተካሄደ።
መድረኩን በይፋ ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ተመጣጣኝና ቀጣይነት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት የመሰረተ ልማት ግብ ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለማህበራዊ ልማት እና ለአገራዊ ብልፅግና መሰረት በመሆኑ ከግማሽ በላይ የሚሆነው ህዝባችን አሁንም የመብራት አገልግሎት ተደራሽ ባለመሆኑ ባለፉት ዓመታት በብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም 1 እና 2 ከግሪድና ከግሪድ ውጪ ተደራሽነትን በማስፋት፣ ተቋማዊ አቅምን በማጠናከር እና ወሳኝ ኢንቨስትመንቶችን በማንቀሳቀስ ረገድ ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል ብለዋል።
አገራችን የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማስፋፋት ማሻሻያ እና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ እቅዶችንም በ80ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ (UNGA80) ብሄራዊ ኢነርጂ ኮምፓክትን በማዘጋጀት ቁርጠኝነቷን አሳይታለች ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም (NEP 3) ስኬታማነት በጋራ በመተባበር፣ እውቀትን በግልፅ በመለዋወጥ እና ጥረታችንን ወደ አንድ የጋራ ሀገራዊ ራዕይ በማቀናጀት ላይ በመወያየት የግሪድ መስፋፋት፣ ከግሪድ ውጪ ላለው ማህበረሰብ የመፍትሄ አቅጣጫዎች፣ ዲጂታላይዜሽን፣ የፋይናንስ ክፍተቶችን፣ የመሠረተ ልማት ውስንነቶችን እና በየሴክተሩ የተጠናከረ ቅንጅት እንዲኖር የሚያመላክት መድረክ ነው ብለዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም የኢትዮጵያን የረዥም ጊዜ የልማት ግቦች የሚደግፍ እና የዜጎቻችንን ህይወት የሚያሻሽል ሁሉን አቀፍ፣ ዘላቂ እና የማይበገር የወደፊት የኃይል አቅርቦትን ለመገንባት የሚያስችል በመሆኑ ከመድረኩ የሚገኙ ገንቢ ሃሳብና አስተያየቶች ለስትራቴጂው መዳበር አስተዋፅኦ ስለሚኖረው ሁሉም የነቃ ተሳትፎ በማድረግ እንዲሳተፉ አሳስበዋል፡፡
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽን መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ዳቢ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ከገንዘብ፣ ከትምህርትና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ በተቋቋመው ብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም የስትራቴጂ ማሻሻያ ግብረ ሃይል የኢነርጂ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ከየሴክተሩ ቁልፍ ተቋማት የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችን ያካተተ የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞ ከ IED ከተባለ አማካሪ ድርጅት ጋር በጋራ በተለያዩ ስራዎች ላይ ከአንድ አመት በላይ ሲሰራበት ቆይቷል ብለዋል።
በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2035 የመሰረታዊ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ የተዘጋጀው ስትራቴጂ ህብረተሰቡን እንዴት ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል፤ ምን ዓይነት ተቋማዊ ቁመናና አደረጃጀት ያስፈልጋል፤ የሚሉ ጉዳዮችን ያካተተ ነው ያሉት አቶ መስፍን ከመድረኩ የተገኙ ግብዓቶችን በማካተት ከዳበረ በኋላ በቀጣይ ወራት በኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን 100% ለማረስ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀውን ስትራቴጂ ከውጪና ከሀገር ውስጥ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች በተገኙበት ይፋ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
በመድረኩ ከማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ የመንግስት ተቋማት ተወካዮች፣ የአለም ባንክ ተወካዮችና ከሶላር ኢነርጂ ልማት ማህበር ተወካዮችናሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ተሳትፈዋል፡፡