በአማራ ክልል በአነርጂ ዘርፍ ለሚከናወኑ ተግባራት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገለፀ።
ባህር ህዳር# መጋቢት 29/2018 ዓ.ም (ው ኢ ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም የሚተገበረው የአዴሌ ኘሮጀክት ባዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ በአማራ ክልል በአነርጂ ዘርፉ ለሚከናወኑ ተግባራት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ዳኝነት ፈንታ(ዶ.ር)፣ ከክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የኤሌክትሪፊኬሽን ዳይሬክተር ከአቶ ታገለ አድማሱና ከሌሎች የዘርፉ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለሙያዎች ጋር በኩሪፍቱ ሪዞርት ተገናኝተው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኢነርጂ ዘርፍ ክልሉን ለማሳደግ የሰጠውን ድርሻ፣ እየተሰሩ ባሉት እንቅስቃሴዎች፣ ለዕድገቱ ማነቆ በሆኑ ጉዳዮችና በተወሰዱ መፍትሔዎችና በሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
በምክክራቸው በርካታ ሃሳቦች ተነስተው የወደፊት የስራ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።
ክቡር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ በአነርጂ ዘርፍ ለሚከናወኑ ማንኛቸውም ተግባራት ከጎን በመቆም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ለሁለት ቀናት ሲካሄድ በቆየው መድረክም ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ባላቸው አጀንዳዎች ዙሪያ ተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን የለገሱ ሲሆን መድረኩን የመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአዴሌ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አዲስዓለም መብራቱና የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የኤሌክትሪፊኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታገለ አድማሱ በምላሻቸው ሰፋ ያለ ማብራራያ ሰጥተዋል።
የመርሃ ግብሩን የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የክልሉ የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ክቡር ኢንጂነር (ዶ/ር) ዳኝነት ፈንታ ሲሆኑ ከዋናው የሃይል መስመር ርቀው የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከጨለማ ለማውጣት አማራጭ ኢነርጂ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ያሉት የጸጥታ ችግሮችም ለስራው እንቅፋት መፍጠራቸውን አመልክተው ነገር ግን እነዚህ ችግሮች ጊዜያዊ በመሆናቸው ወደ ተግባር ለመግባት መዘግየት አይገባም ብለዋል።
በክልሉም ለዘርፉ አስተግባሪዎች በተዘጋጀው መድረክ ተሳታፊዎች በቂ ግንዛቤ እንደተፈጠረላቸውና በፕሮጀክቱ አሰራር ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዳገኙ በመገመት ወደ ስራ እንዲገቡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።