በኢትዮጵያ የኢነርጂ ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ዝግጅት ዙሪያ የግምገማ ግብረ መልስ መድረክ ተካሄደ።
መጋቢት 24/2018.ዓ.ም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የኢነርጂ ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ ያተኮረ የግምገማ ግብረ መልስ መድረክ በክቡር ሚኒስትሩ የስብሰባ አዳራሽ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ ረቂቅ ሰነዱ በገለጻ እንዲቀርብ ጋብዘዋል።
የኢነርጂ ፖሊሲውን ረቂቅ ሰነድ በገለጻ ያቀረቡት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ አቶ አለሙ መንገሻ ሲሆኑ ሃገሪቱ በ1986 ዓ.ም የተዘጋጀውን የኢነርጂ ፖሊሲ ስትጠቀም መቆየቷን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየተደረገ ከሚገኘው የኢነርጂ ዘርፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ይበልጥ ለማጣጣምና ለአሰራር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንዲቻል ነባሩን መከለስ ማስፈለጉን በመግቢያ ንግግራቸው ገልጸዋል።
አቶ አለሙ አስከትለው የፖሊሲውን ይዘት፣ክለሳ ማድረግ ያስፈለገባቸውን መሰረታዊ ምክንያቶች፣ዝግጅቱ ያለፈባቸውን ሂደቶች፣በፓሊሲው የተካተቱ ስድስት አበይት ጉዳዮች፣የፓሊሲው ዋና የውጤት መስክ ፕሮግራምና የክትትልና ግምገማ ማዕቀፍ እንዲሁም የፖሊሲ ሰነዱን አደረጃጀት በዝርዝር አቅርበው ለሚነሱ አስተያየትና ጥያቄዎች ዝግጁ አድርገዋል።
አቶ ሄኖክ አሰፋ የፕሪሳይስ ኮንሰልት ዋና ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው በረቂቅ ሰነዱ ዙሪያ ሙያዊ ድጋፍ በመስጠትና በማማከር ሂደት የተሳተፉ ሲሆን በፓሊሲው ዝግጅት ዙሪያ ግብዓት በመስጠት ረገድ ሌሎች ሃገራትንም ባሳተፈ መንገድ ቁልፍ አስተዋፅኦ ያበረከቱ አካላትን የማንነት መግለጫ በዝርዝር አቅርበዋል።
አያይዘውም ከፓሊሲው ጠንካራ ጎን፣ የሃገራት የኢነርጂ ፍጆታና ገቢ ንጽጽር እንደ ተሞክሮ፣የዘርፉ አተገባበር ስርዓት ፍሰት፣ ከትግበራ ጋር የተገናኙ ተቃርኖዎች፣በኢነርጂ አቅራቢዎች በኩል ያሉ ውስንነቶችና መደረግ ያለባቸውን ለውጦች እና ትኩረት የሚሹ ናቸው ያሏቸውን አራት መሰረታዊ ጉዳዮች ጨምሮ አብራርተዋል።
የቀረበውን ማብራሪያ በመመርኮዝ በበይነ መረብ በተካሄደ የቀጥታ ተግባቦት ከአፍሪካ ሃገራት ተሳትፎ ያደረጉ የኢነርጂ ሴክተሩ ባለሙያዎች ፣የማህበራት ተወካዮችና ሌሎች ለፖሊሲው ማዕቀፍ ይዘት ቁልፍ አስተዋፅዖ ያበረከቱ አካላት ገንቢ አስተያየቶችን ለግሰዋል።
መድረኩ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ዶ/ር ፍፁም አሰፋ የተጋበዙበት ሲሆን ፓሊሲው የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቆራጥነት በማሳየት ለኢነርጂ ዘርፉ ህይወት የሚዘራና ለትግበራ ዝግጁ መሆኑ የተስተዋለበት ሲሉ በአፅንዖት ተናገረዋል።
እንዲሁም ከዚሁ ጎን ለጎን ተያያዥ የሆኑ የህግ ማዕቀፎችን በመቃኘት በማይቃረን መልኩ አካቶ ማዘጋጀት ያስፈልጋልም ሲሉ ክብርት ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው ለፓሊሲው ክለሳ አስተዋፅዖ ያደረጉ አጋር አካላትን አስቀድመው ያመሰግኑ ሲሆን ፓሊሲው በኢነርጂ ዘርፉ የተኬደበትን ረጂም ርቀት ያሳየ ሆኖ አግኝተነዋልም ብለዋል።
አያይዘውም መንግሥት የግሉን ሴክተር በመሳብ ዘርፉን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ተሳታፊ እንዲሆኑ ምቹ መደላድል መፍጠር ይኖርበታል ሲሉም አሳስበዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ እና ሌሎች የበላይ አመራሮች እንዲሁም ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ ከነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተጋበዙ ባለድርሻዎች የተሳተፉ ሲሆን ከሃገሪቱ እድገትና መሠረተ ልማት መሳለጥ ጋር በተገናኘ የኤሌክትሪክ አቅርቦትና ተደራሽነትን ለማስፋት ፖሊሲው አሁን ያለበት ደረጃ ይበል የሚያስብልና የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን በጋራ ያሰመሩበት ጉዳይ ሆኖ ተጠቅሷል።
በቀጣይ በሰነዱ ዙሪያ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን መካተታቸውን ለማየት የሚመለከታቸው አካላትን ባሳተፈ መልኩ መድረክ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።