ከዋና መስመር ርቀው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የአማራጭ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
መጋቢት 24/2018ዓም (ው.ኢ.ሚ) የከዋና መስመር ርቀው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የአማራጭ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ገለጹ፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን ሰላማጎ ወረዳ የወይደይ ሶላር ሚኒግሪድ ፕሮጀክት 200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ 200 ኪሎ ዋት ሀይል የማመንጨት አቅም ያለውና ከ2 ሺህ በላይ አባወራዎችን የሀይል ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በማከል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኤሌክትሪክ ሀይል ሽፋንን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ከዋና መስመር ርቀው ለሚገኙ የገጠሩን የህብረተሰብ ክፍል በአማራጭ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የጸሀይ ሀይልን በመጠቀም ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ከማድረግ አልፎ ተቋማትን የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ በማድረግ በተለይ ጤና ፣የትምህርት እና ሌሎች አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግር እየተቀረፈ መሆኑን አስረድተዋል።
በመጨረሻም ይህ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመተባበር የተሰራውን ፕሮጀክት ህብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቀው አደራ ብለዋል።
በመርሀ ግብሩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ፣የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተወካይ እና የሀገር ሽማግሌዎች መልእክት አስተላልፈዋል ።