ጠንካራ ተቋማዊ አቅም ለመገንባት የሴቶችን እኩልነትና መብት መደገፍ ያስፈልጋል ተባለ፡፡
መጋቢት 9/2018 ዓ.ም.(ው.ኢ.ሚ) ጠንካራ ተቋማዊ አቅም ለመገንባት የሴቶችን እኩልነትና መብት መደገፍ ያስፈልጋል ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሱልጣን ወሊ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ ጊዜ “Give to gain” በሃገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ80ኛ ጊዜ “የሴቶች ድምጽ ለእኩልነት እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን /ማርች 8/ በዓል መርሃ ግብር ላይ በአጽንኦት ተናገሩ፡፡
በማህበረሰቡ ዘንድ አብላጫውን ቁጥር የያዙ እንደመሆናቸው መጠን በማንኛውም የልማት እንቅስቃሴ ሴቶችን ማሳተፍ አማራጭ ሳይሆን አማራጭ የሌለው ምርጫ ነውም ያሉ ሲሆን እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትም ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተጨባጭ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንና ከሶስት ዓመታት በፊትም በነበሩ ተቋማዊ ሪፎርሞች ሴቶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የስራ መደቦች አካታች እንደነበሩ አውስተዋል፡፡
በተለይም በገጠራማው የማህበረሰብ ክፍል ሴቶች ከፍተኛ የሥራ ጫና ያለባቸው እንደመሆናቸው መጠን ከ6-8 ሰዓት የሚደርሰውን ጊዜያቸውን ውሃ ለመቅዳትና ማገዶ ለመልቀም ስለሚያውሉት ለተለያዩ የጤና እክሎች ሲዳረጉ መቆየታቸውንና እየተዳረጉ እንደሚገኙም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስገነዘቡት፡፡
በመሆኑም ከእነዚህ ችግሮች እንዲላቀቀቁ ለማድረግ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል ከመደበኛው የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ በርቀት የሚገኙትን ማህበረሰቦች ተጠቃሚ ለማድረግ በሚኒስቴር ብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን መርሃ ግብር እቀድ ተነድፎ በሶላርና በሚኒግሪግ በማዳረስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ሴቶች ካለፍላጎታቸው ከሚደርስባቸው የጾታ ጥቃት ጋር በተገናኘም የአመለካከትና የባህሪ ለውጥ ላይ መስራት አስፈላጊ ሲሆን ወንዶች ብቻቸውን ታግለው የሚያመጡት ለውጥ ባለመኖሩ የሴቶችን አጋርነት ማመንና መሰረተ ብልጽግናን የሚያረጋግጡ ሴቶች መሆናቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል፡፡
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስርዓተ ጾታ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የውብዳር አሚኖ በበኩላቸው ንፁህ የመጠጥ ውሃና ኃይልን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የሴቶች ሚና የጎላ መሆኑንና ሴቶች የችግሩ ተጋፋጭ ብቻ ሳይሆኑ የመፍትሔውም በመሆናቸው በተግባራቱ የሴቶችን ፍላጎት ከውሃና ኢነርጂ አቅርቦት አንጻር ለመገንዘብ የውይይት አካል ማድረግ፣ የውሳኔ ሰጪነት አቅምን ማሳደግ፣ በቴክኒክና ሙያ ዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ ማበረታታትና የሥራ አካባቢን ለሴቶች ምቹና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው የሚል መልዕክት አስተላፈዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የኬር ኢትዮጵያ ፕሮግራም ማናጀር ወ/ሮ ፍትህ ደመላሸ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስርዓተ ጾታ ዕኩልነት ስትራቴጂን እና የአዴሌ ፕሮጀክት የስርዓተ ጾታ ስፔሻሊስት ወ/ሮ አምሳሉ ሁንዴ የስርዓተ ጾታና የኢነርጂ ቴክኒካል ቡድን የስራ ተግባር ጠቀሜታ፣ሚናና አቅጣጫዎችን ያካተቱ ሰነዶችን በመድረኩ ላይ አቅርበዋል፡፡
በዓሉን አስመልክቶ የፓናል ውይይት የተደረገ ሲሆን የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ የህግ ማዕቀፎችን ማጠናከር፣ በኢነርጂው ዘርፍ ድምጻቸው እንዲሰማ ሰፊ ጥረት ማድረግ፣ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን ማሳደግና ሌሎች አጽንኦት የተደረገባቸው ሃሳቦች በውይይቱ ዳብረው ተገልጸዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የክቡር ሚኒስትር ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ማሙሻ ሃይሉ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፐሮፌሰር ዶ/ር ጌታቸው በቀለ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች በኢነርጂ ዘርፍ ዋና ስራ አስኪያጅ ሃና ጌታቸው፣ ስራ አስፈጻሚዎችና ባለሙያዎች የታደሙበት ሲሆን የዳቦ ቆረሳና የሻማ ማብራት መርሃ ግብርና የስነ ጽሁፍ ስራ ቀርቧል፡፡