ኢትዮጵያ ለዛምቤዚ የውሃ ተፋሰስ ኮሚሽን ልኡካን በአረንጓዴ አሻራ ያላትን የካበተ ልምድ በስፋት እያካፈለች ነው።
መጋቢት 7/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ከዛምቤዚ የውሃ ተፋሰስ ኮሚሽን (zambezi watercource comission)ከፍተኛ ልኡካን ጋር በአረንጓዴ አሻራ ዙሪያ ያላትን ልምድ በስፋት እያጋራች ነው።
የዛምቤዚ የውሃ ተፋሰስ ኮሚሽን (ZAMCOM) ከፍተኛ ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በካፒታል ሆቴል በተዘጋጀ መድረክ በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እንዲሁም የውሃ ተፋሰስ አስተዳደር ተሞክሮን አስመልክቶ ልምድ እያካበቱ ውለዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ለልኡካኑ አስቀድመው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላት የውሃ ድርሻ 86 በመቶ እንደሆነና ይህንን በጋራ ለመጠቀም እንዲቻል ታችኞቹን የተፋሰስ ሀገራት ከግምት በማስገባት እያስተዳደረች መሆኑን አስገንዝበዋል።
አክለውም ሃገሪቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን ከመተግበር አኳያ በመንግስት ተነሳሽነትና በህዝቡ ዘንድ በተፈጠረው ዘመቻ 48 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል ለሽልማት በመታጨቷ ይህ ተግባር እንደባህል የተወሰደና የዓለምን ቀልብ በመሳብ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ እንደቆየ ታሳቢ ሊደረግ የሚገባው ነው ብለዋል።
አያይዘውም የኮሚሽኑ አባላት በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታና ጉብኝት ተጨባጭ ልምዶችን ወደ አገራቸው ይዘው መሄድ እንዳለባቸው በማሳሰብ ኢትዮጵያም ከዛምቤዚ የውሃ ተፋሰስ ኮሚሽን ልምድ ለመጋራትና ለመተግበር ቁርጠኝነቷን አረጋግጠዋል።
የዛምቤዚ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሚስተር ፌሊክስ ሞሲ ንጋምላጎሲ በበኩላቸው በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በዋናነት ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ዙሪያና በአረንጓዴ አሻራ ተግባር ህዝብን በማስተባበር ረገድ የታየው ስኬት ለዛምቤዚ ተፋሰስ አገራት ትልቅ ተሞክሮ እንደሚሆን ጠቁመው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያስመዘገበችው ድልና በጊቤ 3 እና ኮይሻ ባሉ ፕሮጀክቶች የኃይል አቅርቦትና የኢኮኖሚ ዕድገትን ማረጋገጥ መቻሏ ትልቅ ስኬት ነው ሲሉም አድንቀዋል፡፡
በዛምቤዚ ተፋሰስ ውስጥ ካሪባ እና ካቦራ ባሳ የተባሉ ግድቦች ቢኖሩም አሁንም ጥቅም ላይ ያልዋለ ሰፊ የውሃ ሀብት መኖሩን የጠቀሱት ዋና ጸሐፊው የኢትዮጵያ ታላላቅ የመሠረተ ልማት ተሞክሮዎች ለተፋሰሱ አገራት ተነሳሽነት የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።
በመድረኩ ከውሃና ኢነርጂ በኩል ለልምድ ልውውጡ አጋዥ ሰነዶች የቀረቡ ሲሆን በተሳታፊዎቹ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የዛምኮም (ZAMCOM) ልዑክ በኢትዮጵያ በሚኖረው ቆይታም በሀገራቱ መካከል ያለውን የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ትብብር ለማጠናከርና የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመቋቋም የኢትዮጵያን የአካባቢ ጥበቃ እና የውሃ እና ሌሎች የመሰረተ-ልማት ስራዎች እንደሚጎበኝ ይጠበቃል ።