ለተቋሙ ሰራተኞች "ስነምግባራዊ ውሳኔና የጥቅም ግጭትን መከላከል እና ማስተዳደር" በሚል መሪ ሃሳብ ስልጠና ተሰጠ።
የካቲት 25/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ለውሃና ኢነጂር ሚኒስቴር ሰራተኞች "ስነምግባራዊ ውሳኔ እና የጥቅም ግጭትን መከላከል እና ማስተዳደር" በሚል መሪ ሃሳብ ስልጠና ተሰጠ።
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ትልልቅ ፕሮጀክቶችን የሚያስተዳድር በመሆኑ ከሰው ሀብት፣ ከፋይናንስና ከሎጀስቲክ አንፃር ስነምግባርን ተከትለን አገልግሎት መስጠት እንድንችል ስነምግባራዊ ውሳኔ እና የጥቅም ግጭት ምንነትን በአግባቡ ተረድተን እንዴት መከላከልና ማስተዳደር ይቻላል የሚለውን ግንዛቤ እንድንጨብጥ መድረኩ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም የጥቅም ግጭት ምንድነው፣ የጥቅም ግጭት ሙስና ነው ወይስ አይደለም፣ መንስኤውስ ምንድነው፣ እንዴትስ መከላከል ይቻላል፣ የጥቅም ግጭት ወሰኑስ የት ድረስ ነው፣ ተቋማችንስ ለጥቅም ግጭት ተጋላጭ ነው ወይ፣ እንዴት እንከላከል፣ እንዴትስ እናስተዳድር የሚለውን በግልፅ የሚመልስ ነው ብለዋል።
ካለማወቅ የሚጠፋ ጥፋት ከወንጀል ነፃ አያደርግም ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው "የማይወስን ሰው አይምራ" የሚለውን አባባል ለመስበር የስነምግባርራዊ ውሳኔ ምንነትን በአግባቡ በመረዳት ለምንሰጠው ውሳኔ ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ስልጠና በመሆኑ በአግባቡ መከታተልና ግልፅ ያልሆነውንም በውይይት ማዳበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተቋማችን የተጀመረው የሀብት ምዝገባ አዲስ ቴክኖሎጂ፣ ሃሳብና የአሰራር ስርዓት ላይ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል በመሆኑ እንደተቋም ሁሉም ሰራተኛ ሀብቱን በማስመዝገብ ለሌሎች አርአያ ልንሆን ይገባል፤ በሲስተም ሀብቱን ያላስመዘገበ ሰራተኛም እስከ የካቲት 30 ድረስ እንዲያስመዘግቡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ሀብት በበዛ ቁጥር ለሙስና ተጋላጭነትና ተጠያቂነት ስለሚኖር ስልጠናው አስፈላጊ ነው፤ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደታችንን እና የጥቅም ግጭትን በመከላከልና በመምራት ሙስናንና ብልሹ አሰራርን የሚፀየፍ አገልጋይ ማፍራት ይገባል ብለዋል።
የስልጠናውን ሰነድ ያቀረቡት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ስሜ ስነምግባር እንደየሰው አረዳድ የተለያየ ትርጉም የሚሰጠው እንደሆነ ጠቁመው፤ እንደውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ግን የመጠጥ ውሃ፣ የሳኒቴሽንና የኢነርጂ አገልግሎትን መሰረት ያደረገ የጋራ የሆነ ፍቺ ሊኖረው ይገባል ብለዋል።
ውሳኔ የተሻለ አማራጭ የመምረጥና የመተግበር ሂደት በመሆኑ የተቋምን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆን አለበት ያሉት አቶ ጌትነት ውሳኔ ስንሰጥ የተዛባ እንዳይሆን ሰዎችን በማይጎዳ መልኩ ህግን፣ መመሪያንና ደንብን በመከተልና አማራጮችን በማየት መወሰን እንደሚገባ በስልጠናው ሰነድ ላይ አመላክተዋል።
በስልጠና መድረኩ ከተሳታፊዎች ለተነሱ በርካታ ሀሳቦች፣ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የክቡር ሚኒስትር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ማሙሻ ኃይሉ መድረኩን የመሩ ሲሆን በሰፊም ውይይት ተደርጓል።