በኢነርጂ ልማት ዘርፍ በአግባቡ ያልተሰራ ዕቅድ ለሃይል እጥረት መከሰት ምክንያት ስለሚሆን ጥንቃቄ እንደሚሻ ተገለፀ።

በኢነርጂ ልማት ዘርፍ በአግባቡ ያልተሰራ ዕቅድ ለሃይል እጥረት መከሰት ምክንያት ስለሚሆን ጥንቃቄ እንደሚሻ ተገለፀ።   የካቲት 24/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በኢነርጂ ዘርፍ በአግባቡ ያልተሰራ ዕቅድ ለሃይል እጥረት መከሰት ምክንያት ስለሚሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢንጅነር ሱልጣን ወሊ "power flexibility planning"/ተለዋዋጭ ዕቅድን ለሃይል አቅርቦት መጠቀም/በሚል የስልጠና አጀንዳ በራማዳ ሆቴል በተዘጋጀው የአቅም ግንባታ ስልጠና የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር አሳሰቡ።   ክቡር ዶ/ር ኢንጅነር ሱልጣን ወሊ ለማንኛውም ተግባር ዕቅድ ማቀድ የመጀመሪያ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመው ለውጤታማነት ይህ ደረጃ ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃል ብለዋል። እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ከመጣው የሃገሪቱ የህዝብ ብዛትና የኢኮኖሚ ፍላጎት ጋር በተገናኘ በቂ የሆነ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ በሚከናወኑ ተግባራት ጥራት ያለው ዕቅድ ሁነኛ ሚና ስለሚጫወት በዘርፉ ለሚሰሩ ተግባራት በጥንቃቄ አቅዶ መመራት ያስፈልጋልም ብለዋል።   በዕለቱ የሚካሄደው የአቅም ግንባታ ስልጠናም በአማራጭ ኢነርጂ ዘርፉ ለሚተገበሩ ስራዎች ትልቅ አስተዋፅዖ ስለሚኖረው ተግባር ላይ ማዋል ከተሳታፊዎች ይጠበቃል ብለዋል። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የታዳሽ ሀይል አማካሪ የሆኑት አቶ ተመስገን ተፈራ በበኩላቸው ሃገሪቱ የተለያዩ ሃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው ታዳሽ ኢነርጂዎች ስላላት ይህንን ሃይል ከማመንጨት ጀምሮ ወደ ተጠቃሚው ለማድረስ የሚከናወኑ ተግባራትን ለማዘመንና ከጊዜው ጋር ለማሻሻል ስልጠናው መሠረታዊ መሆኑን ጠቁመው ሃገሪቱ በ2030 ተገቢ፣ የዘመነና ዘለቄታዊነቱ የተረጋገጠ የሃይል አቅርቦት ለሁሉም ዜጎች ለማድረስ አቅዳ ለመተግበር ለምታደርገው ጥረትም ወሳኝ ነው ብለዋል።   ስልጠናውን ከሰጡት መካከል የዓለም አቀፉ የታዳሽ ኢነርጂ የሃይል ስርጭት ቡድን መሪ ሚስተር ፍራንሲስኮ ጋፋሮ የሚገኙበት ሲሆን በዘርፉ በተለይም ከነፋስ ሃይል ኤሌክትሪክሲቲ ለማመንጨት በተከናወኑ ተግባራት ዙሪያ ስታስቲካዊ መረጃ በማቅረብ በተለዋዋጭ ዕቅድ የተቃኘ ስራ ለመስራት የሚያስችል ግብዓት መስጠትን ዓላማ ስለሚያደርግ በአቅም ግንባታ ስልጠናው የሚነሱ አጀንዳዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመዋል።   መርሃግብሩን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የታዳሽ ኢነርጂ ኤጀንሲ /International Renewable Energy Agency/ጋር በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን ከውሃና ኢነርጂ ሚ/ር፣  ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል፣ እንዲሁም ከነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን እየተሳተፉበት እንደሚገኙና ለተከታታይ ሶስት ቀናት እንደሚቀጥል ተገልጿል።

Share this Post