"በአድዋ ድል ሉአላዊነታችንን እንዳስከበርን የምግብ ሉአላዊነታችንን ለማረጋገጥም መረባረብ ይጠበቅብናል!"_ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ

"በአድዋ ድል ሉአላዊነታችንን እንዳስከበርን የምግብ ሉአላዊነታችንን ለማረጋገጥም መረባረብ ይጠበቅብናል!"_ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ የካቲት 20/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በአድዋ ድል ሉአላዊነታችንን እንዳስከበርን የምግብ ሉአላዊነታችንን ለማረጋገጥም መረባረብ ይጠበቅብናል ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ አሳሰቡ።   ክቡር ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በሃገር አቀፍ ደረጃ ለ130ኛ ጊዜ "ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ !"በሚል መሪ ቃል የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮችና ሰራተኞች በተለያዩ ሁነቶች በጋራ ባከበሩት የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል መድረክ ላይ ነው። አያይዘውም የአድዋ ድል የመላው አፍሪካውያን ድል የተበሰረበትና የኢትዮጵያ ከፍታ የታየበት የድል ማማ ስለሆነ ልንኮራ ይገባልም ብለዋል።   በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ጉዳይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አርበኛ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ የውሃ ሃብታችንና የኢነርጂ ልማታችን የሃገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ሁነኛ ሚና ስለሚጫወት በዘርፉ ተግተን ልንሰራ ይገባናል ብለዋል።   የድል መታሰቢያ በዓሉን የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ስሜ በበኩላቸው የአድዋ ድል ብሄራዊ ጥቅማችንን የማስከበር ሃላፊነት ለመወጣት መሰረት የጣለና የባህር በር ጥያቄያችንን ለማስመለስም ከበኩራት እንድንንቀሳቀስ የሚያስችል ታሪክ ነው ብለዋል።   በሰነዱ ዙርያ አስተያየታቸውን የሰነዘሩት ተሳታፊዎች በበኩላቸው የሃገሪቱን አንድነትና ህልውና ለማስቀጠል ጀግኖች አባቶቻችን በመጡበት መስመር መጓዝና የወንድማማችነት መንፈስ ማጠናከር ይገባል ብለዋል። በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያም በሚገጥሙን ፈተናዎች እንደምናሸንፍ እርግጠኛ መሆን፣ በሃገራችን ጉዳይ አለመደራደርና በስኬቶቻችን መኩራት ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል ተብሏል።

Share this Post