"የከፍተኛ አመራሩ አርአያነት ለጸረ ሙስና ትግል" በሚል መሪ ቃል ለውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አመራሮች ስልጠና ተሰጠ።

"የከፍተኛ አመራሩ አርአያነት ለጸረ ሙስና ትግል"በሚል መሪ ቃል ለውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አመራሮች ስልጠና ተሰጠ።   የካቲት18/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነጂር ሚኒስቴር አዘጋጂነት ስነ ምግባራዊ ውሳኔ አሰጣጥ እና የጥቅም ግጭትን መከላከልና ማስተዳደር በሚል ጭብጥ ለዘርፉ አመራሮች ስልጠና ተሰጥቷል። የስልጠና መድረኩን በንግግር የከፈቱት የውሃና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የዛሬው የስልጠና መድረክ ዋና ዓላማ የስራ ሀላፊዎችና ሰራተኞች ለዜጎች አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት ከሀላፊነታቸው ጋር በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ የጥቅም ግጭት ውስጥ ሊከታቸው የሚችሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ግጭቱን መከላከል ወይንም በአግባቡ ማስተዳደር እንዲችሉና ሙስናን መከላከል የሚያስችል እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት እንዲያዳብሩ የሚያስችል በመሆኑ ስልጠናውን በሚገባ መከታተል ይገባል ብለዋል። እንደ ተቋም በውሃ እና ኢነርጂ ዘርፍ በርካታ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ የታወቀ መሆኑን የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ የግንባታ ጨረታ ከማውጣት ጀምሮ ለህብረተሰቡ እስከሚደርስ ባለው ሂደት ከውሳኔ አሰጣጥና ከጥቅም ግጭት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለመቅረፍም ሆነ ለማስተዳደር የዚህ ዓይነቱ ስልጠና ወሳኝና ተገቢ ነው ብለዋል። ስልጠናው በሁለት ምእራፍ ተከፍሎ የተሰጠ ሲሆን በመጀመሪያው ምእራፍ ከሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርስቲ ዶ/ር ተስፋዬ ሂርጳሳ በስነ ምግባራዊ ውሳኔ አሰጣጥና የጥቅም ግጭትን አስመልክቶ ውሳኔ እና የጥቅም ግጭት ምንነት፣ ውሳኔ ሰጪዎች በውሳኔ ሂደል ሊከተሉት ስለሚገባ መርህ፣ በስነ ምግባራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ሞዴሎች፣ የጥቅም ግጭት አይነትና መንስኤዎች እንዲሁም የጥቅም ግጭትን ለመከላከል የሚረዱ የህግ ማእቀፎቾ በሚመለከት በዝርዝር ግንዛቤ አስጨብጠዋል።   የሁለተኛው ምእራፍ የስልጠና በዶ/ር የሱፍ ኢብራሂም ከዘርፉ ጋር ተያይዞ የጥቅም ግጭት ተጋላጭነት እና ስጋት እንዲሁም ግጭትን መከላከያ ዘዴዎች በሚመለከት የማወያያ ጥያቄዎችን በማንሳት ጭምር በሰፊው አብራርተዋል። በስልጠና መድረኩ ከተሳታፊዎች በተነሱ በርካታ ሀሳቦች፣ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።   የውይይት መድረኩን የመሩት ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በተነሱ ሀሳቦች ዙሪያ ማብራሪያና አቅጣጫ አስቀምጠዋል። ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን በማብራሪያቸው ስልጠናው ለእያንዳንዳችን ወሳኝና አስፈላጊ በመሆኑ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደታችን ከስነምግባር አኳያ እየቃኘን እንዲሁም የጥቅም ግጭትን በመከላከልና በመምራት ሙስናንና ብልሹ አሰራርን የሚጸየፍ ትውልድ ማፍራት የሁላችንም ግብ ሊሆን ይገባል ብለዋል።   ስልጠናው ከአመራሩ በተጨማሪ እስከታችኛው የዘርፉ መዋቅር ላሉት ሙያተኞች በአጭር ጊዜ ስልጠናው መሰጠት እንዳለበትም አቅጣጫ ሰጥተዋል። የፌደራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የስነ ምግባር ግንባታ ም/ኮሚሽነር ፍቃዱ ሰቦቃ ኮሚሽኑ የዚህ አይነት ስልጠናዎችን ለመስጠት ሲያቅድ 54 ከፍተኛ ምሁራንን ይዞ ሲንቀሳቀስ የነበረ መሆኑን ጠቁመው አሁን ላይ 20 ምሁራንን በመጠቀም በ27 ዘርፎች ስልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል።   ከአሁን በፊት ለአመራሩ በከተማ እና መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ስልጠና የተሰጠ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ የተቋማት የጥቅም ግጭት ተጋላጭነትና መከላከያ ሰልቶች በሚል ጭብጥ እየተሰጠ ያለው ስልጠና አላማው አመራሮች በጉዳዩ ላይ ግንዛቤያቸው አድጎ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል። በውይይቱ ለተነሱ ሀሳብ አስተያየትና ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያም ሰጥተዋል ምክት ኮሚሽነሩ።

Share this Post