ተፋሰስን ማልማት ለኢነርጂና ለመጠጥ ውሀ መሰረት በመሆኑ በአግባቡ ሊሰራበት ይገባል ፡፡ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ

ተፋሰስን ማልማት ለኢነርጂና ለመጠጥ ውሀ መሰረት ድንጋይ በመሆኑ በአግባቡ ሊሰራበት ይገባል፡፡ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ የካቲት 17/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ተፋሰስን ማልማት ለኢነርጂና ለመጠጥ ውሀ መሰረት ድንጋይ በመሆኑ በአግባቡ ሊሰራበት ይገባል ሲሉ በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስቴሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ በአዳማ ከተማ ሂል ሳይድ ሆቴል በአዋሽ ተፋሰስ የ2018 የበጋ ወቅት የውሃ ምደባ የባለድርሻ አካላት የዉይይት መድረክ ላይ ተናገሩ።   ከዚህ አኳያ ያለንን የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ መጠንና ጥራት በጥናት ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑንና በዚህ ዙሪያም በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም የሚቀሩ ስራዎችም አሉ ብለዋል።   አዋሽ ተፋሰስ በአግባቡ ስራ ላይ የዋለ ወንዝ በመሆኑ በአግባቡ ሊጠበቅ ይገባል ያሉት ክቡር አቶ ሞቱማ ኮሚቴው በተፋሰሱ ላይ ያቀዳቸውንና የተሰሩ ስራዎችን የጋራ ማድረግና ወደ ተግባር መቀየር ይገባልም ብለዋል። የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አደን አብዶ በበኩላቸው በዕለቱ የሚካሄደው መርሐ ግብር ለሀገሪቱ ልማት የደም ስር የሆነው የአዋሽ ተፋሰስ ሶስት ግድቦች በከሰም ፣ቆቃና ተንዳሆ ዙሪያ ባለፉት ወራቶች ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድና ሳይንሳዊ መረጃዎችን በመጠቀም ሲሰራ የቆየውን የውሃ ምደባ የጥናት ሂደት ለባለድርሻዎቹ በማቅረብ የጋራ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሚያስችል ነው ብለዋል።   በሂደቱም የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ ያለውን የውሃ ክምችት፣ የዝናብ ትንበያና የተጠቃሚዎችን ፍላጎት በጥልቀት መርምሮ እንደነበር አስታውሰው የውሃ ምደባ ሲካሄድ ሰፋፊ የመስኖ አውታሮችን፣ የስኳር ፋብሪካዎችን የምርት ግብዓቶችን፣ አነስተኛ ተጠቃሚ ማህበራትን እንዲሁም የሴቶችንና የአርብቶ አደሮችን ፍላጐት ባገናዘበ መልኩ እንደሚከናወን ገልፀዋል።   በመድረኩ ላይ ከዘርፉ ጋር በተገናኘ የተለያዩ ሰነዶች ለውይይት የቀረቡ ሲሆን ፍትሃዊና አሳታፊ የውሃ ምደባ እንዲካሄድ፣ የውሃ ጥራትን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት እንዲደረግና ስራዎችን በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተሳታፊዎች አስተያየት ሰተዋል።   ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተቀናጀ የውሀ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ፣የአዋሽ ፕሮጀክት ውሃ ምደባ አስተባባሪ፣ ፕሮጀክቶች ማናጀሮች፣ የውሃ ምደባ ተጠቃሚዎችና ሌሎች ባለድርሻዎች በመድረኩ ተሳትፈዋል ።

Share this Post