የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያዩ።
አዲስ አበባ # የካቲት 17/2018 ዓም ውኢሚ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ /Sem Fabrizi/ ከተመራ ልዑክ ጋር በዘርፉ በትብብርና በቅንጅት ለመስራት በሚቻሉ ጉዳዮች ዙሪያ በጥልቀትና በዝርዝር ተወያይተዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ የልዑካን ቡድኑን ተቀብለው ሲወያዩ ኢትዮጵያ ከለውጡ ወድህ በተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ተፋሰሶችን በማስተዳደር ፣ታለቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በርከታ ግድቦችን በመገንባትና በማጠናቀቅ በዘርፉ ውጤታማ መሆን እነደቻለች ገልጸዋል ።
ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ደረጃውን የጠበቀ የሳኒቴሽን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑንና ውጤት መታየቱንም አብራርተዋል
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየተተገበረ ባለው በባዘርኔት/BaSRINET ፕሮጀክት የዜጎችን በተለይ የአርብቶአደሩንና የከፊል የአርብቶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል በመስኖ ልማት፣የውሃ አካላትን በመንከባከብና በማጎልበት ፣የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራና ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን አላማ አድርጎ በመስራት ውጤት መምጣቱን ተናግረዋል
በአረንጓዴ አሻራ እንደ ሀገር ከ48 ቢልዮን ችግኞች በላይ በመትከል የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አካባቢን ከመፍጠር ባሻገር በምግብ እራስን የመቻል ስራም የተሰራበት ፕሮጀክት መሆኑን አብራርተዋል ።
ዶ/ር ሀብታሙ አክለው በኢነርጂው ዘርፍም በርካታ ስራዎች ተሰርተው እንደሀገር የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ በኬኒያ፣ሱዳን፣ታንዛኒያና በሌሎችም ሀገራት ተደራሽ እየተደረገ እንዳለ ገልፀው በሚታዩ ክፍተቶች ሁሉ ከጣልያን መንግስት ጋር አብረን በትብብር ለመስራት ግንኙነታችንን እናጠናክራለን ብለዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በውይይቱ ላይ ተገኝተው ኢትዮጵያ በኢነርጂ ዘርፍ ዕምቅ አቅምና ሀብት እንዳለት ገልፀው በጨለማና በኋላቀር አኗኗር እየተሰቃዬ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ስራዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራ አንዳለና ውጤትም የታየበት መሆኑን ገልፀዋል።
ዶ/ር ሱልጣን አክለው ከዚህ ቀደም በዘርፉ በሚጠበቀው ደረጃ ውጤት እንዳይታይ ክፍተት ይታይባቸው የነበረ የፋይናናንስ አስተዳደርና የፖሊሲ ጉዳዮች ማሻሻያ ተደርጎባቸው መፍትሄ እንዳገኙ ገልፀው ከጣሊያን መንግስት ጋር አብሮ ለመስራት ምቹ ሁኔታዎች አሉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ /Sem Fabrizi/ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ ዘርፉም ይሁን በአጠቃላይ እያሳየች ያለውን ፈጣንና ሁለንተናዊ ዕድገት አድንቀው የጣሊያን መንግስትን በመወከል በቀጣይ በዘርፉ ከቀድሞ በበለጠ ሁኔታ ግንኙነትን በማጠናከር በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በመጨረሻም የልዑካን ቡድኑ አባላት ከክቡር ሚኒስትሩ እጅ ስጦታ ቀብለዋል፤ዲጂታል ኤግዚብሽኑንም ጎብኝተው አድናቆታቸውን ገልፀዋል።