ኢትዮጵያ ከፀሃይ ሃይል ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅሟን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እያከናወነች መሆኑ ተገለፀ።
የካቲት 10/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ኢትዮጵያ ከፀሃይ ሃይል ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅሟን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች እያከናወነች ነው ሲሉ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ክቡር
ዶ/ር ሱልጣን ወሊ (ኢ/ር) ገለፁ።
ሚንስትር ዴኤታው ይህንን ያሉት በዚሁ ሳምንት በሶማሌ ክልል ግንባታቸው ተጠናቆ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት በጀመሩት የሶላር ሃይል ማመንጫ ኘሮጀክቶች የምርቃት መርሃ ግብር ላይ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ለመጡ ባለሙያዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።.
በሃገሪቱ ከዋናው መስመር በከፍተኛ ርቀት ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማገዝ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ የብድር ድጋፍ በሚኒግሪድ መስመር ዝርጋታና በሶላር ሆም ሲስተም ለማዳረስ በስፋት እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ እንደ ሃገር የፀሃይ ሀይልን በመጠቀም ኤሌክትሪክ ለማመጨት እንደ ሃገር በተሰሩ ስራዎች እስከ አሁን ድረስ ተደራሽነቱ ከ10 በመቶ ያልበለጠ መሆኑን በአፅንዖት የተናገሩት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው
ያለንን እምቅ የታዳሽ ሃይል ጥቅም ላይ በማዋል የሃይል ተደራሽነትን ለማስፋት ሰፊ ስራ የሚጠይቅ በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዘርፉ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ የሚቀጥልበት መሆኑን ተናግረዋል።
በሃገሪቱ እያደገ ከመጣው የኢኮኖሚ ፍላጎትና የህዝብ ብዛት ጋር ተያይዞ ለተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ሃይል መጠቀም አስገዳጅ እየሆነ በመምጣቱ የ13 ወር ፀጋ የሆነችውን ሃገር የፀሃይ ሃይል በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባልም ብለዋል።
በዕለቱ በክልሉ በዶሎ ዞን 250 ኪሎዋት የሚያመነጨውና በ170 ሚሊዮን ብር የተገነባው የምርቃን የሶላር ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ
ለ1120 የከተማዋ አባወራዎች የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የከተማዋ ነዋሪዎችም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ስላደረጋቸው የተሰማቸውን ደስታ በተለያዩ ሁነቶች አንፀባርዋል።