የውኃ እና ኢነርጂ ሚንስቴር ሚንስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በዓለም ባንክ የዓለም አቀፍ ኦፕሬሽን ዋና ዳይሬክተር አና በጀርዴን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
የካቲት 6 /2018ዓም (ው.ኢ.ሚ.) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ሉኡካኑን ባነጋገሩበት ወቅት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከሌሎች የፌደራል ተቋማት እና አጋር ድርጅቶች ጋር እየተሰሩ ባሉ ፕሮግራሞች እና ፕሮጀክቶች ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ ጋር አያይዘውም የዓለም ባንክ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋር በሚሰራቸው የውኃ እና ኢነርጂ ፕሮጀከቶች የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ዜጋ በር ያንኳኳ መሆኑን፤ በኢነርጂ ዘርፍም እየተሰሩ ያሉ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እና የሥርጭት ሥራዎች እንዲሁ ከሀገራችን አልፎ የጎረቤት ሀገራትን ተጠቃሚ ያደረጉ መሆናቸውን እና እነዚህ ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች በቀጠናው ላሉት ሀገራት የትብብር እና የቅንጅት ሥራዎች አይነተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ክቡር ሚንስትሩ በማያያዝም አሁን ባለው ከፍተኛ ህዝብ ቁጥር እና ተደራሽ ያልሆነ ማህበረሰብ ጋር ተያዞ ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ ስፋት እና ፍላጎት አንጻር እጅግ ግዙፍ ተጨማሪ መዋዕለ ነዋይ የሚያስፈልግ መሆኑን በአጽኖት ገልጸዋል፡፡
በዓለም ባንክ የዓለም አቀፍ ኦፕሬሽን ዋና ዳይሬክተር አና በጀርዴ በበኩላቸው ባንኩ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚያደርገው የብድር እና ድጋፍ በጀት በውኃውም ሆነ በኢነርጂው ዘርፍ የተሰሩ ሥራዎች እጅግ በጣም አመርቂ እና ለሌሎች ሀገራትም በምሳሌነት ተቀምረው ሊቀርቡ የሚችሉ መሆናቸውን በአድናቆት በመግለጽ በተሰሩት ሥራዎች እና በፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በማከልም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በውኃና ኢነርጂ ዘርፍ በቀጣይ ለምትሰራቸው ሥራዎች የባንኩ ድጋፍ የማይለያት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአለም ባንክ ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሚያገኘው ድጋፍና ብድር በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን፣በውሃ ሀብት አስተዳደር ፣በኢነርጂ፣በጎርፍ መከላከል እና በሜቲወሮሎጂ ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።