በተለያዩ አምዶች ተከፋፍሎ በተዘገጀው የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎረም ስልጠና ተሰጠ።
የካቲት 03/2018 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ለተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በተለያዩ አምዶች ተከፋፍሎ በተዘገጀው የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎረም ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።
የዕለቱ ስልጠና የሚያተኩረው "የመንግስት ሰራተኞች የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ስርዓት መገንባትና የማስፈፀም አቅም ማሳደግ" ፣ "ፈጣንና ተደራሽ የመንግስት አገልግሎት ግንባታ" እና "የፕሮግራም በጀት አዘገጃጀት ፣ አጠቃቀምና አፈፃፀም"በሚሉ አምዶች ላይ መሆኑ ታውቋል።
የስልጠናውን መርሃግብር የማስጀመሪያ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የአብይ ኮሚቴ ፀሐፊ አቶ ኦልቀባ ባሼ የሪፎርሙ ትልቁ አላማ ብቃትን ከሪፎረም ተግባራት ጋር በማገናኘት በተቋሙ የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት ነው ብለዋል።
አያይዘውም የሪፎርሙ ስራ በአግባቡ ተግባራዊ ሲሆን ብቃት በተግባር ይረጋገጣል፣ ተቋማት ትክክለኛውን ባለቤት ያገኛሉ፣ ለውጥን ከራሱ የሚጀምርና በተግባር የሚያሳይ ፈፃሚና አመራር ይፈጠራል ብለዋል።
አክለውም የሪፎርሙ ስራ ውጤታማ እንዲሆን የሚመደበውን በጀት በውጤት የሚያሳይ፣ሙስናን እጅግ የሚፀየፍና የሚቃወም፣ ለሚፈጠሩ ችግሮች ተጠያቂና ሀላፊነት የሚወስድ አመራርና ፈፃሚ መፍጠር የግድ ይላልም ብለዋል።
በተጨማሪም የሪፎርሙ ፍኖተ ካርታ ሁሉንም አመራርና ፈፃሚ ባለቤትነት ስለሚጠይቅ ለውጡ የራሴ ነው በሚል ስሜት ሰልጣኞች ስልጠናውን ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉ በቬርቿል ለሚከታተሉ ሰልጣኞችም ጭምር አሳስበዋል።
አቶ በላይነህ ይርዳው "የመንግስት ሰራተኞች የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ስርዓት መገንባትና የማስፈፀም አቅም ማሳደግ" በሚለው አምድ ዝርዝር አፈፃፀሙን በሚገልፅ ሁኔታ የተዘጋጀን ሰነድ ለሰልጣኞች አቅርበዋል ሰፊ ማብራሪያም ሰጥተዋል።
አቶ መኮንን ዓለሙ "ፈጣንና ተደራሽ የመንግስት አገልግሎት ግንባታ" በሚለው አምድ ላይ ዝርዝር አፈፃፀምና ሰፊ ይዘት ያለውን ሰነድ ለሰልጠኞች ከማብራራያ ጋር አቅርበዋል።
አቶ ኑረዲን መሃመድ በተሰጣቸው ጊዜ "የፕሮግራም በጀት አዘገጃጀት ፣አጠቃቀምና አፈፃፀም" በሚል አምድ ስር የተዘጋጀን ሰነድ ስለበጀት ምንነት፣ አጠቃቀምና ውጤታማነት ምን ማለት እንደሆነ በስፋት በማብራራት አቅርበዋል።
ስልጠናውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች፣ የቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤት እና የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ሰራተኞች ፊት ለፊትና በቨርቿል ተሳትፈዋል።
በቀረቡ ሰነዶችና በአጠቃላይ በሪፎርሙ አተገባበር ዙሪያ ሰልጣኞች በርካታ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተው ከመድረክ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።