ክቡር ሚኒስትሩ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ልኡክ ጋር በትብብር ለመስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መከሩ።

ክቡር ሚኒስትሩ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ልኡክ ጋር በትብብር ለመስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መከሩ። የካቲት 2/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ልኡክ ጋር በትብብር ለመስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል። ክቡር ሚኒስትሩ በነበራቸው ቆይታ ልኡካኑ ላነሷቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።   ክቡር ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በውሃ ሀብት አስተዳደር፣ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም በኢነርጂ ልማት ዋና ዋና ዘርፎች ተዋቅሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ውሃ ለሁሉም ልማት መሰረት መሆኑን የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ ዘላቂ እና አስተማማኝ የሆነ የውሃ ሀብት እንዲሰፍን እንደሀገር ባለፉት አመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውንና በዚህም መሰረት በውሃ ሀብት መጠን መጨመር፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ባለፉት ሁለት ዓመታት ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን አስረድተዋል።   ከንጹህ መጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ተግባራት ጋር በተያያዘም በተለይም ገጠራማ የሆኑ አካባቢዎችን ተደራሽ ለማድረግ በአለም ባንክ ድጋፍ ተጨባጭ ስራዎች መከናወናቸውንም ክቡር ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። በማከልም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኢኒሼቲቭ በሆነው የ"ግድቤን በደጄ" ፕሮጀክት የውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ተምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት ላይ የዝናብ ውሃን ዘመናዊ በሆነ መንገድ በማጠራቀም በሶላር ፓምፕ አማካኝነት እንዲጠቀሙ በማድረግ በውሃ እጥረት ምክንያት የሚደርሰውን ተጽእኖ ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።   ከሀይል አቅርቦት ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ሀይል ተደራሽ እያደረገች እንደምትገኝ እና ከዋናው የኤሌክትሪክ ሀይል ርቀው የሚገኙ የኢትዮጵያ አካባቢዎችን በሶላር ሀይል ተጠቃሚ የማድረግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ክቡር ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ልኡካኑ ከክቡር ሚኒስትሩ ጋር ስላደረጉት ውይይት በማመስገን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በጋራ ሊያሰሩ የሚችሉ በርካታ አነሳሽ ጉዳዮች እንዳሉ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

Share this Post