የአካባቢውን ማህበረሰብ የመብራት ጥያቄ የሚመልሰው ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

የአካባቢውን ማህበረሰብ የመብራት ጥያቄ የሚመልሰው ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመረ።   ጭሮ:-የካቲት /2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በጋራ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ በቡርቃ ዲምቱ ወረዳ የሃሮ ጉራቲ እና የሃዊ ጉዲና ቡርቃ ኦዳ የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የአካባቢውን ማህበረሰብ የመብራት ጥያቄን ምላሽ የሚሰጠው ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመረ።   በዓለም ባንክና በኢትዮጵያ መንግስት ወጪ የተገነባውን ፕሮጀክት በይፋ ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በሃሮ ጉራቲ 210 ኪሎ ዋት እና በቡርቃ ኦዳ 132 ኪሎ ዋት የሚያመነጨው የፀኃይ ሀይል ፕሮጀክት የአካባቢውን ማህበረሰብ የዘመናት የመብራት ጥያቄን ምላሽ የሚሰጥ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።   ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በሃሮ ጉራቲ በ160 ሚሊዮን ብር ከ703 በላይ አባወራዎች እና በቡርቃ ኦዳ በ140 ሚሊዮን ብር ወጪ ከ507 በላይ አባወራዎች ተጠቃሚ የሚያደርገው ፕሮጀክት ለረጅም ዓመታት አግልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ የአካባቢው ማህበረሰብ እንደራሱ ንብረት እንዲንከባከብ አሳስበው፤ አስተዋፅኦ ያበለከቱ አካላትንም አመስግነዋል።   የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ተወካይ እና የሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ፕሮግራም አቅርቦት ዳይሬክተር ኢ/ር ጥላሁን ብርሃኑ ገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል። በመርሃ ግብሩ የም/ሐረርጌ ዞን ተወካይ፣ የውሃና ኢነርጂ ፅ/ቤት ኃላፊ፣ የሃሮ ጉራቲ እና የቡርቃ ኦዳ ቀበሌ ነዋሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

Share this Post