በፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ

በፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው። ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ   አርሲ/ነንሰቦ:-ጥር 29/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ።   በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን የነንሰቦ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት /Solar Mini-grid Project/ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑን ያበሰሩት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በተቋሙ ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚኖሩ የገጠር ማህበረሰብ ክፍሎችን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።   ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ሀገር ናት ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂን መጠቀም የተሻለ አማራጭ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ተወካይ እና የሀገርአቀፍ የኤሌክትሪክ ፕሮግራም አቅርቦት ዳይሬክተር ኢ/ር ጥላሁን ብርሃኑ ከአጋር አካላት በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ የገጠሩን ማህበረሰብ ማህበራዊ ተቋማትን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ተብለዋል።   በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን አስተዳደር አቶ በሪሶ ባሜ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እስከሚበቃ ድረስ አስተዋፅኦ ያበረከቱ አካላትን አመስግነዋል። 365 ኪሎ ዋት የሚያመነጨው የናንሰቦ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከአፍሪካ ልማት ባንክና ከኢትዮጵያ መንግስት በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በጋራ የተገነባ ሲሆን 824 ቤተሰቦችን፣ የጤናና የትምህርት ተቋማትንም ጨምሮ ተጠቃሚ ያደርጋል።   በመድረኩ የኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን አስተዳዳሪ፣ የናንሴቦ ወረዳ አስተዳዳሪ፣ የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል የስራ ኃላፊዎች፣ የአካባቢው ነዎሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።

Share this Post