ኢትዮጵያ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ አንድም ብር ብድርና ዕርዳታ አልወሰደችም፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)

ኢትዮጵያ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ አንድም ብር ብድርና ዕርዳታ አልወሰደችም፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)   ጥር 26/2018 (ው.ኢ.ሚ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንድም ብር ብድርና እርዳታ ሳንወስድ ያሳካነው ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ታላቁ የሕዳሴ ግድባችን በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ቁርጠኛ አቋም ተገንብቶ የተጠናቀቀ ነውም ብለዋል፡፡   ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጨክነው በቁርጠኝነትና በጋራ ሆነው ስለሰሩ የተከወነ ፕሮጀክት መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁ የሆነውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መገንባቷን ጠቅሰው፤ በዚህም ሳታበቃ ከአፍሪካ ሦስተኛ የሆነውን የኮይሻ ኃይል ማመንጫ እየገነባች መሆኑንም አንስተዋል፡፡   ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አክለውም ህዳሴን ካለአንድ ብር ብድርና ዕርዳታ ያሳካ መንግስት እና ህዝብ ፕሮጀክት አይሰራም ማለት አይቻልም ብለዋል። በተመሳሳይ ባለፊት 6 ወራት ውስጥ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች የኢነርጂ አጠቃቀም ብቻ 16 በመቶ እድገት ማሳየቱን ገልፀው፤ ወደ አምስት የሚጠጉ በሶላር ኢነርጅ ዘርፍ የሚሰሩ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውንና በቀጣይ ዓመት ሙሉ በሙሉ ስራ እንደሚጀመሩ ጠቁመዋል፡፡   በቀጣይ ዓመትም ከሶላር ምርት ብቻ 900 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

Share this Post