የአዋሽ ተፋሰስ አስተዳደር ፅህፈት ቤት በውሃ ምደባ ማህበራዊ አካታችነት ላይ ትኩረት ያደረገ የጥናት ሰነድ ግኝት የግምገማ መድረክ ተካሄደ፡፡
ጥር 25/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአዋሽ ተፋሰስ አስተዳደር ፅህፈት ቤት በውሃ ምደባ ማህበራዊ አካታችነት/social inclusion/ላይ ትኩረት ያደረገ የጥናት ሰነድ ግኝት የግምገማ መድረክ በጌት ፋም ሆቴል ተካሄደ።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሚገኙ ዋና ዋና ዘርፎች መካከል የተፋሰስ አስተዳደር ዘርፍ በሃገራችን ያለው ውሃ ዘላቂ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ የሚውልበትን አግባብ የሚወስን ዘርፍ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት የሚሻ ነው ያሉ ሲሆን ሌሎች ትላልቅ ተፋሰሶች የሚነሱትም ከዚሁ በመሆኑ የአዋሽ ተፋሰስ እድለኛ ነው ለማለት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
አያይዘውም በተለይም የውሃ ምደባ ተግባር በፖሊሲ የተደገፈና በየጊዜው እያደገ በመምጣቱ ምክንያት የሁሉንም ፍላጎት ባማከለ መልኩ እንዲከናወን ለማስቻል ከተጠናው የጥናት ሰነድ ግኝት በመነሳት ተሳታፊዎቹ የመፍትሄ ሃሳብ እንዲሰነዝሩ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡
የአዋሽ ተፋሰስ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደን አብዶ በበኩላቸው የአዋሽ ተፋሰስ ጽ/ቤት በዋናነት የሚያከናውናቸው ተግባራት በዋናት የውሃ ምደባ ስርዓት ማስፈን፣የውሃ ጥራትን መቆጣጠር፣የጎርፍ አደጋን መቆጣጠርና ተፋሰስን መከላከል ሲሆን በውሃ ምደባ ተግባር ፍትሃዊና ሁሉንም አካታች በሆነ መልኩ ለማከናወን እንዲቻል በዕለቱ ከሚቀርበው ጥናታዊ ግኝት በመነሳት ቀደም ሲል ለነበሩት ክፍተቶች መፍትሄ ለማፈላለግ መድረኩ ያስችለናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አክለውም የአዋሽ ተፋሰስ በክረምት ጊዜ ከፍተኛ የጎርፍ ስጋት ያለበት የሰው ልጆችን እስከማፈናቀል እንደሚደርስና በቀሪዎቹ ስምንት ወራት ውስጥ ደግሞ ከፍተኛ የውሃ እጥረት የሚከሰትበት መሆኑን አውስተው ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከተንዳሆ፣ከከሰምና ከቆቃ ግድቦች ቀደም ሲልተቆጥበው የተያዙ የውሃ ክምችቶችን በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግም አስቀድሞ በጥናት የተለዩ ክፍተቶች የተባሉትን የቋንቋ እና የጾታ አካታችነትን ከግንዛቤ በማስገባት ሂደቱ የሚከናወን መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንዲሁም በውሃ ምደባ ሂደቱ ተጠቃሚዎች ደግሞ አርብቶ አደሮች፣አርሶ አደሮችና ኢንዱስትሪዎች በመሆናቸው የፍላጎት መጠናቸውን ከግንዛቤ በማስገባት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ይሆናል ሲሉ አቶ አደን ጠቅሰዋል፡፡
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአዋሽ ብሉ ዲል ፓርትነርሺፕ የውሃ ምደባ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ግዛው በበኩላቸው የአዋሽ ተፋሰስ የውሃ ምደባ ማህበራዊ አካታችነት መረጃ ለመሰብሰብ የተደረገውን የጥናት ሂደት ሲያብራሩ በቅድሚያ 123 ጥያቄዎች ተዘጋጅተው ለ59 የውሃ ተጠቃሚዎችና ለ67 የመንግስት ተቋማት እንዲደርሱ በማድረግ የተገኘውን ግኝት ለመተንተንና ለአካታችነት እንቅፋት የሚሆኑ 25 ክፍተቶች በመለየታቸው ከነዚሁ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን አምስት ጉዳዮች በማስቀደም ችግሩን በመፍታት በቀጣይ ፍትሃዊ የውሃ ምደባ እንደሚካሄድ አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም አቶ ጌታቸው በአጽንኦት እንደገለጹት ይህንን መሰል ጥናቶች በርካታ ሂደቶችን አልፈው የሚመጡ እንደመሆናቸው መጠን ግኝቶቹ በሌሎች አጋር አካላት ተቀባይነትን አግኝተው መሬት ላይ ወርደው የማህበረሰቡን ችግር መቅረፍ ስለሚገባቸው የውሃ ምደባ ተጠቃሚዎች ያነሷቸውን ክፍተቶች በመሙላት ሂደት ሁሉም ባለድርሻ ሊረባረቡበት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
መርሃ ግብሩ የብሉዲል ፕሮጀክት ከኔዘርላንድ መንግስት ጋር በጋራ በመሆን ያዘጋጀው ሲሆን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አማካሪዎች፣በአዋሽ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ አጋር አካላት፣የኦሮሚያና አፋር ክልል ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል፡፡