የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ላይ ስልጠና ተሰጠ::

የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ላይ ስልጠና ተሰጠ።   ነቀምቴ : ጥር 15/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ላይ ለባለድርሻ አካላት ስልጠና እየተሰጠ ነው። ስልጠናውን የሰጡት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ሰራ አስፈጻሚ እና የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የአብይ ኮሚቴ አባልና ጸሀፊ አቶ ኦልቀባ ባሼ መንግስት ለዜጎች የሚሰጠው አገልግሎትና የሚመራበት ቢሮክራሲያዊ ሂደት የሀገር ህልውና በመሆኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትንና ሂደቶችን በማሻሻል የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ሪፎርሙን በሚገባ ማከናወን ይገባል ብለዋል።   ባለፉት ዓመታት የሪፎርም ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም የፖሊሲ ክፍተት፣ ባህላዊ ጫና፣ የአመራር ጥራት፣ የቴክኖሎጂ ዝግመት፣ ተቆራኝቶ አለመሄድ፣ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ የተለያዩ ተቋማት አንድ አይነት የለውጥ መሳሪያ ስልት የመጠቀም፣ ከለውጡ ስኬቶች ይልቅ በለውጥ መሳሪያዎች አተገባበር ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ፣ የአፈጻጸም ግምገማን ከተጠቃሚነት እና ከተጠያቂነት ጋር አለማገናኘት እንዲሁም የለውጥ ስራዎችን ቀጣይነት ሳይኖራቸው በዘመቻ መልክ ማከናወን ሪፎርሙ ስኬታማ ሳይሆን የቀረባቸው ምክንያቶች መሆናቸውን አቶ ኦልቀባ በዝርዝር አስረድተዋል።   ቀልጣፋ፣ ውጤታማና ተደራሽ አገልግሎት ለዜጎች ማቅረብ፣ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት የነገሰበት የአሰራር ስርዓት መዘርጋት፣ ብዝሃነትና አካታችነትን ያረጋገጠ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት፣ ነጻ ገለልተኛና በብቃት ላይ የተመሠረተ ፕሮፌሽናል ሰራተኛ ማፍራት፣ ለአገራዊ የልማት ግቦች ስኬት ጉልህ አስተዋጽኦ ማድረግ፣ የህግ የበላይነትና የሞራል ልእልናን በሲቪል ሰርቪሱ ማስፈን እንዲሁም ዜጎችን ማገልገል የክብር ምንጭ መሆኑን የሚያምን ሠራተኛ መፍጠር የራፎርሙ አላማዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።   የስትራቴጅክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚና የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ሪፎርም የዋናው መስሪያ ቤት ቴክኒካል ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሁም የዝግጅቱ አስተባባሪ የሆኑትን አቶ አለሙ መንገሻ እንደዘርፍ በዝግጅት ምእራፍ የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር አቅርበዋል። እንደ ሀገር በሁለተኛው ምድብ ወደ ሪፎርም ከገቡ ተቋማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አንዱ መሆኑን የገለጹት አቶ አለሙ በዝግጅት ምዕራፍ መከናወን ያለባቸውን ሰነዶች ለማዘጋጀት ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ስራ ከተገባ መቆየቱን ገልጸዋል።     የሪፎርም ኮሚቴው ስልጠና ወስዶ በመጀመሪያው ዙር በቢሾፍቱ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት በነበረው ቆይታ ከ15 በላይ ሰነዶች ተዘጋጅቸው ለማንጅመን ቀርበው ከተገመገሙ በኋላ ወደ ሁለቸኛው የሪፎርም ሰነድ ዝግጅት እንደተገባና በአጠቃላይ እንደ ዘርፍ ከአርባ በላይ ሰነዶች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። ሰነዶቹ በቀጣይ በምዘና ሂደት ውስጥ አልፈው የዘርፉን አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ያሳካሉ በሚል እሳቤ እየተዘጋጁ መሆኑንም አብራርተዋል።   ሰነዶቹ ሙሉ በሙሉ ተዘጋጅተው ሲጠናቀቁ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የምዘና ሂደት ተደርጎባቸው ወደ ትግበራ ይገባልም ብለዋል። ዘርፉ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ስታንደርዳቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ያሉት አቶ አለሙ ወደ መሶብ አገልግሎት ቢገቡ የዘርፉን አሰራር ያቀላጥፋሉ የተባሉ አገልግሎቾች ተለይተው በአመራሩ ውሳኔ እንደሚሰጥባቸውም ነው የገለጹልን።   እንደ ሀገር ከ120 ዓመታት በላይ የቆየውን የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት በተሻለ የህዝብን ጥቅም እና ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ ለመተግበር መሠረታዊ የሆነ ሪፎርም እየተካሄደ ነው ያሉት አቶ አለሙ ሪፎርሙ አጠቃላይ የሁሉንም ድጋፍ እና እገዛ የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። በዚህም መሠረት የክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮዎች በሀገርም ሆነ በተቋም ደረጃ ምን እየተሰራ እንዳለና አጠቃላይ የሪፎርሙን እንድምታ በሚመለከት ግልጸኝነት እንዲኖራቸው የተዘጋጀ የስልጠና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ነውም ብለዋል።   በመጨረሻም ሪፎርሙን ማገዝና ለውጤት ማብቃት የሁላችንም ሀላፊነት እና አደራ መሆኑን አውቀን ለውጤታማነቱ የሚጠበቅብንን ሁሉ መፈጸም ይገባናል ሲሉ አቶ አለሙ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። የፌደራል እና የክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የስራ ሀላፊዎች እና የሚመለከታቸው አካላት በስልጠናው እየተሳተፉ ነው።

Share this Post