ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የአዳማ ከተማ የፍሳሽ ማጠሪያ ፕሮጀክት የግንባታ ስራን በይፋ አስጀመሩ።
አዳማ ፡ ታህሳስ 23/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የአዳማ ከተማ የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታን በይፋ አስጀምረዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ በፕሮጀክቱ ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ መቀሌላይ ያስጀመርነውን የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት አዳማ ላይ ለማስጀመር በመገኘታችን ከፍተኛ ደስታ ተሠምቶናል እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ።
ፕሮጀክቱ ከአለም ባንክ በተገኘ 1.9 ቢሊን ብር በሚሆን ወጭ ተገንብቶ በቀጣዮቹ 18 ወራት ይጠናቀቃል ብለዋል።
በተቀመጠው ጊዜ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተቋራጩና አማካሪው ትልቁን ድርሻ የሚወስዱ ቢሆኑም አባገዳዎች፣ እናቶች በአጠቃላይ በመተባበርና በማገዝ ቁርጠኛ የሆነው የአዳማና የፕሮጀክቱ አካባቢ ማህበረሰብ ንብረቶች ሲንቀሳቀሱ በማገዝ፣ በመጠበቅ አንድም ችግር ሳይፈጠር ፕሮጀክቱ እንዲጠናቀቅ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ያላቸውን መተማመንም ገልጸዋል።
የመጠጥ ውሃና የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች በእኩል ሲተገበሩ የሚፈለገው ውብ፣ ማራኪ፣ ጽዱና ለንሮ ምቹ የሆነ ከተማ ይፈጠራል ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ቆሻሻን ማስወገድ ካልቻልን ከተማ ከተማነቱ ቀርቶ የበሽታ ማእከል ይሆናል ብለዋል።
የአዳማ ከተማ ውብ ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ እየተገነባ እንዳለ የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ ለዚህ ደግሞ ክቡር የከተማው ከንቲባ እና አመራሮችን አመስግነዋል።
በአዳማ ከተማ በርካታ ስራ ፈላጊ ወጣቶች እንዳሉ የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ በፕሮጀክቱ በተለያየ የስራ መስክ ከጥበቃ ጀምሮ በማደራጀት ተሳታፊ እንዲሆኑ ቢደረግ ለውጤታማነቱ አስተዋጽኦው የጎላ እንደሚሆን ከ ገልጸዋል።