የዘርፉን ባለሙያዎችና ሀላፊዎች ቴክኒካል ክፍተቶችን በመሙላት በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ውጤታማ ስራ ለመስራት የሚያስችል ስልጠና ነክ ወርክሾፕ እየተካሄደ ነው።

የዘርፉን ባለሙያዎችና ሀላፊዎች ቴክኒካል ክፍተቶችን በመሙላት በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ውጤታማ ስራ ለመስራት የሚያስችል ስልጠና ነክ ወርክሾፕ እየተካሄደ ነው። አዲስአበባ# ታህሳስ 22/2018 ዓ/ም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዜርኔት እና የብሉዴል ፕሮጀክቶች በቅንጅት ባዘጋጁት ለ3 ተከታታይ ቀናት የሚቀጥል የዘርፉን ባለሙያዎችና ሀላፊዎች ቴክኒካል ክፍተቶችን በመሙላት ውጤታማ ስራ ለመስራት የሚያስችል ስልጠና ነክ ወርክሾፕ በማዜኪ ሆቴል እያካሄደ ነው።   የመርሃግብሩን ይፋዊ መጀመር የገለፁት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዜርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሞላ ረዳ የአቅም ግንባታ ስልጠናው ከዚህ ቀደምም ይሰጥ እንደነበረ ገልፀው ስልጠናው ቴክኒካል ክፍተቶችን ለመሙላት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዱለው ተናግረዋል። አቶ ሞላ እንደተናገሩት በዕለቱ የሚቀርቡ ሰነዶችም ይሁን ውይይቶች የሚያተኩሩት በቀሰም፣በተንዳሆና በቆቃ ተፋሰሶችና ግድቦች ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች በጥልቀት በመወያየት የጋራ መረዳት ላይ ለመድረስ ነው ብለዋል። ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የሚተገብራቸው ቁልፍ ተግባራት በሙሉ በውሃ ላይ የተመሰረቱ ናቸው ያሉት አቶ ሞላ ስራዎቹ በሙሉ ቀጣይነትና ውጤታማነት እንዲኖራቸው በበቂ መረጃ ላይ የተመሠረተ የውሃ ምደባና ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍልና አጠቃቀም ማስፈንም አለብን ብለዋል።   በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሉዴል የአዋሽ የአጋርነት የውሃ ምደባ ፕሮጀክት ማኔጀር አቶ ጌታቸው ግዛው በበኩላቸው ውሃ ውድና አለቂ ሀብት በመሆኑ በብዙ ጥንቃቄ በፍትሃዊነት ለተጠቃሚዎች ለመመደብና ለማከፋፈል የሚያስችል ቴክኒካል አቅም ለመገንባት ታስቦ የተዘጋጀ ወርክሾፕ እንደሆነ ገልፀዋል። አቶ ጌታቸው አክለው ስራው በጥናት የተደገፈና በእውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን አዋሽ ተፋሰስ የሚገኝባቸው የአደማ እና የሰመራ ዩኒቨርስቲዎች የዘርፉ ምሁራን የቴክኒካል ኮሚቴ አባላት በመሆን በትብብርና በቅንጅት እየተሰራና እየተመራ መሆኑንም ገልፀዋል።   በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የውሃሀብትና መስኖ ምህንድስና ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልከሪም በደዊ የቆቃ ግድብ ያለበት ተጨባጭ ሁኔታ ፣ክፍተቶችና የመፍትሄ ሀሳቦችን የያዘ ሰነድ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል ። በቀጣይ ቀናት የሰመራ ዪኒቨርስቲ ምሁረንም በከሰምና በተንዳሆ ግድቦች ላይ የጥናት ሰነዳቸውን እንደሚያቀርቡና ተሳታፊዎች በጥልቀት በመወያየት የጋራ መረዳት ላይ እንዲደርሱ እንደሚያግዝም ተገልጿል ።

Share this Post