ሶስት አማካሪዎች ከአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ጋር የውል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ሶስት አማካሪዎች ከአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ጋር የውል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ታህሳስ 23/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከሶስት አማካሪዎች ጋር የውል ስምምነት ተፈራረመ፡፡   የውል ስምምነቱን ያካሄዱት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ናቸው፡፡ ክቡር አምባሳደር ገለጻ በጽህፈት ቤታቸው በተካሄደው የፊርማ ስነስርዓት እንደገለጹት የማህበረሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ ከተያዙት 110 ፕሮግራሞች በ55ቱ ወረዳዎች ከሚገነቡት መካከል እስከአሁን ድረስ የ22 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመገባደድ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከ82,000 የማህበረሰብ አባላት በላይ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንና ለ88 የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን ስራ ከ32 አማካሪ ድርጅቶች ጋር ቅጥር ተፈጽሟል ብለዋል፡፡   በዚህ መሰረት በዕለቱ በ18 ሳይቶች (4 በኦሮሚያ፣4 ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣4 ጋምቤላ እና 6 በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት)በፕሮጀክቱ ለሚካሄዱ ግንባታዎች የውል ስምምነት ፊርማ የተደረገ ሲሆን አማካሪዎቹም ተርን ኮንሰልታንሲ፣ጄቪ ሚልቶ ኢንጂነሪንግ እና ላሊፍቱ ጄኔራል ዴቨሎፕመንት የተባሉት ድርጅቶች ናቸው፡፡   የስምምነቱ ዋና ዓላማም የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት በሚተገብራቸው የግንባታ ስራዎች የጥናትና ዲዛይን እንዲሁም የክትትል ተግባር እንዲያከናውኑ ለማስቻል ሲሆን አማካሪዎቹ ስራቸውን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ከጥራት ጋር እንዲያከናወኑ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው ክቡር አምባሳደሩ ከአደራ ጋር አሳስበው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በማንኛውም መንገድ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡   አማካሪዎቹ በበኩላቸው በአገልግሎት ቆይታቸው ፕሮጀክቱ በታለመለት ጊዜ እንዲከናወን ለማድረግ ግዴታችንን እንወጣለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ለአማካሪዎቹ ተከፋይ የሚሆነው ጥቅል የውል ዋጋ 239,092,458.57 ብር ወይም 1,825,017.83 ዶላር ሲሆን ወጪው ሙሉ በሙሉ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚሸፈን ሲሆን ለአገልግሎቱ የተቀመጠለት የውል ጊዜ በሚቀጥሉት 12 ወራት የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡

Share this Post