የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ጥበቃ ስራን በተሻለ ንቅናቄ ለመምራት የሚያስችል የትግበራ ስምምነት ተፈረመ።

የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ጥበቃ ስራን በተሻለ ንቅናቄ ለመምራት የሚያስችል የትግበራ ስምምነት ተፈረመ። ሠመራ ፡ ታህሳስ 22/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በባዘርኔት ፕሮጀክት በታችኛው የአዋሽ ተፋሰስ ላይ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ጥበቃ ስራን በተሻለ ንቅናቄ ለመምራት የሚያስችለውን የትግበራ ስምምነት ተፈራርማል።   ስምምነቱን የፈረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ የባዘርኔት ፕሮጀክት በመጀመሪያው ምእራፍ እየተገበረ ያለው የአቅም ግንባታና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በመሆኑ በክልሉ ያሉ አካላትን በፕሮጀክቱ አተገባበር ላይ ያላቸውን አቅም ማጠናከርና ማዘጋጀት በእጅጉ አስፈላጊ ነው ብለዋል። በዚህም መሠረት ከወዲሁ ዝግጅት ያስፈልገዋል ተብሎ የተለየው የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ጥበቃ ስራ ከአረንጓዴ ልማት ፣ ከችግኝ ተከላና እና ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር የተቆራኘና የተለየ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ በተሻለ ንቅናቄ ለመምራት የሚያስችል የትግበራ ስምምነት ተደርጓል ብለዋል።   በስምምነቱ መሠረትም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ክትትል በማድረግ ፣የቤዚን አስተዳደር ቅ /ጽ/ቤት በቅርበት ሆኖ በመተግበር እና በመደገፍ እንዲሁም የክልሉ የግብርና ቢሮም በመደገፍና በማስተባበር በቅንጅት ሰፊ ስራ ለመስራት የሚያስችል ነውም ብለዋል። በቀጣይም ከውሃ ምደባ እና ከመረጃ ስርዓት ጋር ተያያዥ የሆኑ ሌሎች ተመሳሳይ የትግበራ ስምምነቶች ይደረጋሉ ብለዋል።   ስምምነቱን የአፋር ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ም/ኃላፊ አቶ አሮን አሊ ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አሰፈጻሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ እና የአዋሽ ተፋሰስ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደን አብዶ ተፈራርመዋል። የአዋሽ ተፋሰስ ቅ/ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደን አብዶ ተፋሰሱ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት አብዛኛው ክፍሉ ደረቅ በመሆኑ የውሃ ማፋሰሻው ካልተጠበቀ ወንዙ በደለል የሚሞላ መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የውሃ ሀብት አስተዳደሩ እንዴት እንደሚመራ ግንዛቤ ማስጨበጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።   የታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ከተለያየ ቦታ የሚመጣ ውሃ የሚሰበሰብበት እንደመሆኑ የውሃ ሀብቱን ከመጠቀም ባለፈ እጥረቱ እንዴት እንደሚከሰት የግንዛቤ ክፍተት መኖሩን በመገምገም ክፍተቱን ሊሞላ የሚችል የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የውይይት መድረክ ከፌደራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ያሉ ባለድርሻ አካላትን ወጣቶችንና የሀገር ሽማግሌዎችን ባሳተፈ መልኩ ተካሂዷል ብለዋል። ውሃን ጥቅም ላይ ለማዋል ስናቅድ ችግሮችን እየለየን መፍትሄ እያበጀን እንሄዳለን ያሉት ኃላፊው ይህንን ለማድረግ ከአካባቢ ጥበቃ ፣ ከግብርና ከመስኖና ቆላማ ጋር በቅንጅት ሁሉም የድርሻውን ወስዶ ሲተገብር የማህበረሰቡ ተጠቃሚነት ይረጋገጣል ፤ የፕሮጀክቱ ዋና አላማም ይሄ ነው ብለዋል።   የባዘርኔት ፕሮጀክት የተፋሰሱን አቅም ለመገንባት አስቻይ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በተፋሰሱ ያሉ ችግሮች ተቀርፈው የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የውሃ ሀብት አስተዳደር ላይ ግንዛቤ ማስጨበጥ የፕሮጀክቱ አንዱ ክፍል ሆኖ እየተተገበረ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

Share this Post