ውሃ የጋራና ውድ ሀብት በመሆኑ መሰረተ ልማቱን በማዘመን ሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ።

ውሃ የጋራና ውድ ሀብት በመሆኑ መሰረተ ልማቱን በማዘመን ሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ። ታህሳስ 21/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሀብት ማዕከል /WLRC/ ጋር በጋራ በመቐለ የፀባ-ዓይና ንዑስ ተፋሰስ ላይ የሚተገበረው የብራት ፕሮጀክት በተሰራው የዳሰሳ ጥናት ዙሪያ በሚካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ውሃ የጋራና ውድ ሀብት በመሆኑ መሰረተ ልማቱን በማዘመን ሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ።   በመድረኩም ከቀረቡ ጥናቶች መካከል የፆታ አካታችነት አንዱ ሲሆን፤ ስለውሃም ሆነ ስለመሬት ሲነሳ የሴቶችና የወጣቶች ሚና ምንድነው የሚለውም ከነተግዳሮቶቹ ቀርበው ውይይት ተደርጎበታል። ብሔራዊ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ብዙነህ አስፋው የውሃ ሀብት ብክነትን ለመቀነስ በቀጣይ በቤዚኑ ሰፊ ስራዎችን ለመስራት የሚጠቁም መድረክ ነው ብለዋል።   ውሃ በባህሪው ተንቀሳቃሽ ነው ያሉት ዶ/ር ብዙነህ በላይኛውና በታችኛው ቤዚን ተጠቃሚዎች መካከል ያለግጭት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር ቤዚኖችን ለማስተዳደር ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ብለዋል። ዶ/ር ብዙነህ አክለውም በቤዚኑ በርካታ የመስኖ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም የውሃ ተጠቃሚዎች ማህበር የላቸውም፤ ለዚህም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተዘጋጁ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ክልሎች በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ስትራቴጂና የአስተዳደር አቅጣጫዎች በማስቀመጥ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በአግባቡ መምራት ይችላሉ ብለዋል።   በቀረበው ጥናት የፀባ-ዓይና ንዑስ ተፋሰስ የመጠጥ ውሃ መሰረተ ልማቶች ጥገና ላይ ቢሆኑም መዘግየት ስላለ የሚመለከታቸው የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም በመፍትሔ አቅጣጫ ላይ ተመላክቷል። በተከዜ ቤዚን የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ችግሮች የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ውስንነት፣ ተከታታይ የክትትልና ግምገማ ስርዓት አለመኖር፣ የግንዛቤ ውስንነት፣ ትክክለኛ መዋቅራዊ አደረጃጀት አለመሮሩ ከተነሱ ተግዳሮቶች የሚጠቀሱ ሲሆኑ ውሃ የጋራና ውድ ሀብት በመሆኑ መሰረተ ልማቱን በማዘመን ሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባም ተገልጿል።

Share this Post