የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆኑ ተገመገመ።
ታህሳስ 17/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎች በጥሩ ሁኔታ እነተካሄዱ መሆኑን የአብይ ኮሚቴ አባላት በቢሾፍቱ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ተገኝቶ ከቴክኒካልና ንዑስ ኮሚቴ አባላት ጋር ገምግሟል።
በእለቱ በየአምዱ ተዘጋጅተው በቀረቡ ሰነዶችና አጠቃላይ በዝግጅት ምእራፉ የተከናወኑ ተግባራት ላይ ጥያቄዎች አስተያየቶችና ሃሳቦች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪና የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የአብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ የተነሱ ሀሳቦች ላይ በሚገባ ማየትና ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ገልጸው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች በተቻለ መጠን በወቅቱ ውሳኔ እያገኙ የሚመሩበት አሰራር የተቀላጠፈ እንዲሆን የሪፖርትና ገምገማ ስርዓቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል።
ከተጠሪ ተቋማት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራርና ግንኙነት መልካም መሆኑንም ክቡር አቶ ሞቱማ ገልጸዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚና የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የአብይ ኮሚቴ አባል እና ጸሀፊ አቶ ኦልቀባ ባሼ የሪፎርሙ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በአግባቡ እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው የተሰሩ ስራዎች ለአብይ ኮሚቴ ቀርበው ከተገመገሙ በኋላ ለሚመለከተው አካል የሚቀርቡበት ስርዓት ተዘርግቶ እየተተገበረ ነው ብለዋል።
ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም በየጊዜው ክትትልና ድጋፍ ማድረጉ የሪፎርሙን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በሚጠበቀው አግባብ ለማከናወን አጋዠ ነው ብለዋል።
የሚዘጋጁ ሰነዶች አንድ ቦታ ላይ መቀመጥ ስላለባቸው ደረጃውን የጠበቀ ክፍል እንደሚዘጋጅና ተጠሪ ተቋማትም በዚሁ መልክ ማዘጋጀት እንዳለባቸው አቶ ኦልቀባ ጠቁመዋል።
ከሰነድ ዝግጅት ጎን ለጎን መሬት ላይ በተጨባጭ የሚከናወኑ ተግባራት መኖራቸውን የገለጹት አቶ ኦልቀባ ምቹ የስራ አካባቢ ከመፍጠር አኳያ የካፍቴሪያ ፣ የህጻናት ማቆያ እና የሸማቾች አገልግሎትን የማጠናከር ስራዎችን እየሰራን መሄድ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ውጤት የተቋማት ድምር ውጤት በመሆኑ እንደዘርፍ የሚዘጋጁ ሰነዶች በተጠሪ ተቋማት በኩልም በዚሁ ልክ እንዲዘጋጁ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱ በእጅጉ ጠቃሚ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎት አስተዳደር ሪፎርም የአብይ ኮሚቴ አባል ዶ/ር ታመነ ኃይሉ የዝግጅት ምእራፍ ስራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆኑ የቀረበው ሪፖርትና የተዘጋጁ ሰነዶች ማሳያ ናቸው ብለዋል።
በአጠቃላይ እንደ ዘርፍ ያለው መደጋገፍና ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።
እንደ ዘርፍ የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎች ተጠናቀው ወደ ምዘና ለመግባት የሚያስችሉ ከ40 በላይ የሰነዶች ዝግጅት ሰራ ወደ መጠናቀቅ ደረጃ መድረሳቸው በየአምዱ በቀረቡ ሪፖርቶች ተገልጿል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ እና የአብይ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በግምገማ መድረኩ ተገኝተዋል።