በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዘርኔት ፕሮጀክት የአቅም ግንባታ ስልጠና እያካሄደ ነው

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዘርኔት ፕሮጀክት የአቅም ግንባታ ስልጠና እያካሄደ ነው ህዳር 9/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የባዘርኔት ፕሮጀክት ትግበራ አካል የሆነውና በአውሮፓ ህብረት የሚደገፈው የአቅም ግንባታ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ማዶ ሆቴል እየተካሄደ ነው፡፡   በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ እንደገለጹት ስልጠናው በጂኦሎጂካል ኢንፎርሜሽን መረጃ ትንተናና በመሬት ቅኝት ዙሪያ የሃገራችንን ወሳኝ የሆነ ቴክኖሎጂ ለማስተዋወቅ የሚጀመርበት መርሃ ግብር መሆኑን ገልጸዋል ፡፡   በቅርቡም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተፋሰስ አስተዳደር ተፋሰስ ክትትል ስትራቴጂ እየተዘጋጀ በመሆኑ የሳተላይት መረጃዎችን በመጠቀም የተሻለ የመረጃ ሽፋን ለመስጠት እንዲቻል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የሚቻልበትን አቅም ለመፍጠር የአቅም ግንባታ ስልጠናው ያስችላል ብለዋል፡፡   አያይዘውም በአሁኑ ወቅትም ከጎርፍ ተጋላጭነት ጋር በተገናኘ ምቹ የሆኑና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችንም ለመለየት ያስችላል፡፡ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዘርኔት ፕሮጀክት ብሄራዊ አስተባባሪ አቶ ሞላ ረዳ ፕሮጀክቱ በአውሮፓ ህብረት የሚደገፍና በጣሊያን ፕሮጀክት አስፈጻሚነት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተጀመረ አንድ ዓመት ማስቆጠሩን አስታውሰው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በተፋሰስ አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች የሚስተዋለውን የአቅም ክፍተት ለመሙላት በተለያየ ጊዜና አጀንዳ ዙሪያ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡   ሚስተር ማርኮ ላንዲ በአውሮፓ ህብረት የባዘርኔት ፕሮግራም አስተባባሪ እንደተናገሩት በሃገሪቱ በውሃ፣በአካባቢና በኢነርጂው ዘርፍ በሚሰሩ ስራዎች ከሚኒስትሪው ጋር በመተባበር በአጋርት ሲሰሩ መቆታቸውን አስታውሰው በተለይም በአቅም ግንባታና በአዳዲስ የቴክኖሎጂ አቅርቦት ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡   ፕሮጀክቱ በዋናነት ትኩረት የሚያደርግባቸው ተፋሰሶችም ዋቢሸበሌ፣የታችኛው አዋሽ እና ደናክል መሆናቸውን ሚስተር ማርኮ አስገንዝበዋል፡፡ በአቅም ግንባታ ስልጠና መድረኩ ላይ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ከተፋሰስ ጽህፈት ቤትና ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሺያል ኢንስቲቲዩት የተውጣጡ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በሌሎች አጀንዳዎች ዙሪያ ለተከታታይ ሶስት ቀናት እንደሚቆይ ተመልክቷል፡፡

Share this Post