ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ የኢንዱስትሪ ፍሳሽ ቆሻሻን የማጣራትና መልሶ የመጠቀም የውሃ ጥራት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ።

ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ የኢንዱስትሪ ፍሳሽ ቆሻሻን የማጣራትና መልሶ የመጠቀም የውሃ ጥራት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ። ጅማ:-ህዳር 6/2018 ዓ.ም (ውኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚተገበረው ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ የውሃ ጥራት መቆጣጠሪያ ከእሸት ቡና መፈልፈያ የሚወጣን ፍሳሽ ቆሻሻን የማጣራትና መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ቴክኖሎጂ /Nature Based Solution/ ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ።   በተቋሙ የገፀ ምድርና የከርሰ ምድርን ውሃ ሀብት የመጠበቅና የማስተዳደር ስራ ይሰራል፤ ያሉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢኮ-ሀይድሮሎጂ ባለሞያ አቶ ወንድወሰን አበጀ በጅማ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ብዙ ጊዜ ከኢንዱስትሪ የሚወጡ ፍሳሾች የውሃ አካላትን የሚበክሉ በመሆኑ ቅሬታዎች ይቀርቡ እንደነበረ አስታውሰው፤ ከአመታት በፊት በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ወደአዊቱ ወንዝ የሚለቀቀውን ፍሳሽ ናሙና በመውሰድ የውሃ ጥራት ቁጥጥር እየተደረገ እንደሆነ ገልፀዋል።   አቶ ወንድወሰን አክለውም ተፈጥሮን መሰረት ያደረገው ተግባር ተኮር ኢኮሃይድሮሎጂ ሳይንስ ተግባራዊ በማድረግ የውሃ ጥራትና መጠን የማሻሻል እና የመቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂን /Nature Based Solution/ በማላመድ የቡና አቅራቢ ነጋዴዎች ቡናውን ካጠቡ በኋላ ወደወንዝ የሚለቁት እና የከርሰምድር ውሃው የተበከለ በመሆኑ በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት የሚያመጣ ከመሆኑም በላይ እንቦጭን ጨምሮ ለመጤ አረሞች መስፋፋት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።   ስለውሃ ጥራት ሲነሳ ፊዚካልና ኬሚካል ይዘቱ የራሱ የሆነ ስታንዳርድ አለው ያሉት አቶ ወንድወሰን ተፈጥሮን በማጤን የብክለት አይነትና መጠኑን በመለየት በሙከራ ደረጃ ተሰርቶ ውጤታማነቱን ለማስፋት የተፈጥሮ ዕፅዋት ዝርያዎችን በመምረጥ በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ቤዚን አባያ ጫሞ ላይ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑንም አክለው፤ ቴክኖሎጂው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከሀብትና ከጊዜ አንፃርም ከ2010 ጀምሮ በዝቅተኛ ወጪ ተግባራዊ እንደሆነም አብራርተዋል። የጅማ ከተማ ንግድ ፅ/ቤት የቡና ጥራትና ገበያ ቁጥጥር የስራ ሂደት መሪ አቶ መንበሩ ኪቲላ በበኩላቸው በጅማ ዞን ትላልቅ የቡና ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ገልፀው፤ በውሃ ብክለት ዙሪያ ከህብረተሰቡ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ምላሽ የሰጠ ቴክኖሎጂ በመሆኑ ህብረተሰቡን ከጉዳት ለመታደግ ሚዲያዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ቴክኖሎጂውን የማስተዋወቅ ስራ በሰፊው ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።   አዲሱን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ወደ ውሃ አካላት የሚለቀቀውን ፍሳሽ ተጣርቶ መለቀቁንም በየጊዜው በባለሞያዎች ክትትል ይደረጋል ያሉት አቶ መንበሩ፤ የቀይ ቡና መፈልፈያው ድርጅት የውጪ ምንዛሪ ከማስገኘቱም ባሻገር ለሴቶችና ወጣቶች የስራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።   በጅማ ከተማ የቀይ ቡና መፈልፈያ ድርጅት ባለቤትና የቡና አቅራቢ ነጋዴ አቶ መሀመድ ጀማል የቀይ ቡና መፈልፈያው ከ10 ዓመት በፊት ስራ የጀመረ ቢሆንም ከቡና ማጠቢያው የሚወገደው ፍሳሽ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ አስነስቶ ለተወሰነ ጊዜ ስራው ተቋርጦ እንደነበር ገልፀዋል።   አቶ መሀመድ አክለውም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አማካኝነት ተፈጥሮን መሰረት ያደረገው ቆሻሻን የማጣራትና መልሶ የመጠቀም ቴክኖሎጂን ተግበራዊ በማድረጋቸው ከአመታት ወዲህ ውጤታማስራ በመስራት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ ዕድል እንደፈጠሩ ገልፀው፤ በሚኒስቴር መ/ቤቱ ስለሚደረላቸው ክትትልና ድጋፍም አመስግነዋል። የግልገል ጊቤ 1 ገባር ወደሆነው አዊቱ ወንዝ የሚለቀቀው ውሃ ከኬሚካል ነፃና በተፈጥሮ መንገድ እያጣሩ እንደሚለቁ በስፍራው በመገኘት ለማየት ተችሏል።

Share this Post