የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የዝግጅት ምእራፍ ስራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው፡፡
ቢሾፍቱ ፡ ህዳር 05/2018 ዓ. ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርምን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የዝግጅት ምእራፍ ስራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ ነው፡፡
እንደ ሀገር ወደ ሪፎርም ከገቡ ተቋማት መካከል የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አንዱ ሲሆን ዘርፉ በኢኮኖሚያዊ ፣ በማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገት የሚጠበቁበትን ግቦች ለማሳካት የሰው ሀብት ትልቁን ድርሻ ስለሚይዝ ይህ ሀብት የሚመራበት ስርዓት በብቃት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የአገልግሎት አሰጣጡንም ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ወደ ሪፎርም ተገብቷል፡፡
እንደ ዘርፍ ሪፎርሙን በውጤታማነት ለመተግበር በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የሚመራ የአብይ ኮሚቴ ፣ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላትን እና በስሩ ደግሞ በርካታ ንኡስ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ከመስከረም /2018ዓ.ም ጀምሮ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡
የሪፎርሙ የዝግጅት ምዕራፍ ለአንድ ዓመት በርካታ ሰነዶችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ተያያዥ ጉዳዮች የሚተገበሩበት ሲሆን ኮሚቴው ከጥቅምት 10/2018ዓ.ም ጀምሮ በቢሾፍቱ ብቃትና ስራ አመራር ኢንስቲትዩት በ25 ቀናት ውስጥ በርካታ ሰነዶችን ማዘጋጀት ተችሏል፡፡
ለሪፎርሙ ተግባራዊነት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በበላይነት ከመምራት ባለፈ በቴክኒካልና ንኡስ ኮሚቴ ደረጃ እየተተገበረ ያለውን እና ያጋጠሙ ችግሮችን በአካል በመገኘት ክትትል አድርገዋል፡፡
ሐሙስ ህዳር 4 ቀን 2018 ዓ.ም ብቃትና ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ቢሾፍቱ ማዕከል ከጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም በየቴክኒካል እና ንዑሳን ቴክኒካል ኮሚቴዎች የተሠሩ ሥራዎች በተደራጀ መልኩ ለአባላቱ እና ለአብይ ኮሚቴ በማቅረብ የጋራ ተደርጓል።
የሪፎርሙ ሥራዎች በሁሉም አምዶች በዕቅዱ መሠረት እየተተገበሩ መሆኑን በውይይቱ በቀረቡ አሥራ አምስት ሰነዶች ገለጻ መረዳት ችሏል።
በሁሉም የኮሚቴ አባላት መካከል ያለው የሥራ ፍላጎት፣ ቅንጅት እና ቁርጠኝነት በየቀኑ እየጨመረ መምጣቱም በግምገማ መድረኩ ተገልጿል።
ስራዎችን በተቀላጠፈ መንገድ በጥራት ለማከናወን እንቅፋት የፈጠሩ ጉዳዩች መኖራቸው በውይይት መድረኩ የተነሳ ሲሆን ችግሮችን ለመቅረፍ የበላይ አመራሩ የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ በቀጣይነት የሚፈልግ መሆኑ ተገልጿል።
በሌላ በኩል ደግሞ የዝግጅት ምዕራፍ ሥራ ለአንድ ዓመት የሚቆይ እንደመሆኑ ወደ መስሪያ ቤት ስንመለስ የመስክ ስራን ጨምሮ የተለያዩ የቤት ሥራዎች ለኮሚቴዎች አባላት ሊሰጣቸው ይችላል የሚል ስጋት ስላለ የሪፎርም ሥራዎች ወደኋላ እንዳይቀሩ እንደ አለፉት ሃያ አምስት ቀናት ምቹ የሰነድ ዝግጅት ቦታ ተመቻችቶ ውጤታማ የሪፎርም ሥራ እንዲሠራ ቢደረግ የሚል ሀሳብም ከኮሚቴዎች ቀርቧል፡፡
በ25 ቀናት በነበረው የዘርፍ ሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍ በየአምዱ የሚጠበቁ ሰነዶች መዘጋጀታቸው የኮሚቴውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ እና እንደ አጠቃላይ የነበረው ተነሳሽነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የአብይ ኮሚቴ አባላት አሳውቀዋል፡፡
በተዘጋጁ ረቂቅ ሰነዶች ላይ በተደረገው ግምገማም ከየንኡስ ኮሚቴው ለተነሱ አንዳንድ ጥያቆዎች በሰነድ ዝግጅት ወቅት ባጋጠሙ ችግሮች እና አጠቃላይ ስለነበረው ሂደት የአብይ ኮሚቴው ምላሽና አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በቀጣይም ሊተገበሩ የሚገባቸው ጉዳዮችን ከወዲሁ እየታሰበባቸው እንዲተገበሩ አብይ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡
በመጨረሻም ያለምንም መንጠባጠብ እስከ ምሽቱ 4:00 ሰዓት በመቆየት የሪፎርሙን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ በከፍተኛ መነሳሳት እና ቁርጠኝነት እየሠሩ ያሉ እና ዛሬም በተደራጀ መልክ ገለጻ ቀርቦ ከሁሉም አባላት ጋር የጋራ ማድረግ እንዲቻል ሁኔታን ላመቻቹ ለኮሚቴ አባላት ምስጋና ተችሯል።