በጥናት ላይ በመመስረት የጎርፍ ውሃን ከጉዳት ወደ በረከት መቀየር እንደሚቻል ተገለፀ።
አዳማ:ህዳር 01/2018 ዓ/ም ውኢሚ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዘላቂና ውጤታማ የጎርፍ መከላከል ስራ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የመነሻ የጥናት ውጤት ጥናት ባደረገው አማካሪ ድርጅት በኩል ቀርቦ ለግምገማና ለውይይት ይፋ ሆኗል።
አማካሪ ድርጅቱ ውል ከገባበት ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ያደረገውን ጥናት የመጀመሪያ ግኝት ሪፖርት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፣ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ቀርቧል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የጎርፍ አደጋን በጥናት ላይ ተመስርቶ በአግባቡ በማስተዳደር ወደ ዕድልና ውጤት መቀየር እንደሚቻል ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሁሉም ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ ተፋሰሶች አካባቢ ሰፊ ስራ ተሰርቶ ውጤታማ መሆን እንደተቻለ የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ በቀጣይ የጥናት ግኝቱን መነሻ በማድረግ በዕውቀት በመስራት ችግርንና አደጋን ወደ ዕድልና መልካም አጋጣሚ መቀየር እንደሚቻል ገልፀዋል።
ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ አክለው የጎርፍ አደጋ በአግባቡ መከላከልና ማስተዳደር ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እና የስነልቦና ችግሮችን የመፍታት አቅም እንዳለው ገልፀው በሚኒስቴር መስሪያቤቱ በተሰራው ስራ የብዙ ዜጎች ህይወትና ሰፊ መሬት መታደግ እንደተቻለ ተናግረዋል ።
በመጨረሻም የጥናት ግኝቱን ያቀረበውን አማካሪ ድርጅቱን አመስግናው ተሳታፊች ግኝቱ ላይ ጠቃሚ አስተያየት እንዲያቀርቡ እና አማካሪ ድርጅቱም የሚነሱ አስተያየቶችን በቅንነት ተቀብሎ የጥናቱ አካል እንዲያደርግ አሳስበዋል።
የጥናቱን ግኝት ያቀረበው ኒኮላስ ኦ-ዲዋየር/NICHOLAS O'DWYER/ የጥናቱን ጽሑፍ የተለያዩ አቅራቢዎች ተከፋፍለው አቅርበው ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው በአማካሪ ድርጅቱና በክቡር ሚኒስትሩ ምላሽ፣ ማብራሪያና የወደፊት አቅጣጫ ተሰጥቷል።