በሚኒግሪድ ሶላር ኢነርጂ አቅርቦት ለሚሰማሩ የግል አልሚዎች የብድር አቅርቦት ለማመቻቸት እገዛ የሚያደርግ ስልጠና መመቻቸቱ የሚበረታታ መሆኑን ተሳታፊዎች ገለጹ
ጥቅምት 28/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በሚኒግሪድ ሶላር ኢነርጂ አቅርቦት በግሉ ዘርፍ ለሚሰማሩ አልሚዎች የብድር አቅርቦት ለማመቻቸት በሚደረገው ጥረት ሙያዊ ሃላፊታቸውን እንዲወጡ ስልጠናው እገዛ እንደሚያደርግላቸው ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡
ተሳታፊዎች ይህንን ያሉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዩኤንዲፒ ፕሮጀክት አማካኝነት በሶላር ሚኒ ግሪድ ተከላ ስራ በሚሰሩ ስራዎች የግል አልሚዎችን ተሳትፎ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የግል ባንኮችና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የብድር አቅርቦት ለማመቻቸት እንዲችሉ ለአስፈፃሚ አካላት በተሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ ነው።
ከኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ የዘላቂ ልማት ሲኒየር ኤክስፐርት የሆኑት አቶ ኪዳኔ ለማ ስልጠናውን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት መንግስት ማህበረሰቡን ከጨለማ ለማውጣት በሶላር ሚኒግሪድ ተደራሽ ለማድረግ በሚተገብራቸው ስራዎች የባንክ ኢንዱስትሪውን ለማሳተፍ በተደረገው የግንዛቤ ፈጠራ በርካታ ልምዶችና ተሞክሮዎች እንዳገኙ ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም የሃርቡ ማይክሮ ፋይናንስ የግብርና እሴት ሰንሰለት ብድር ሲኒየር ኤክስፐርት አቶ ኤልያስ አበበ እንደገለጹት በተለይም የሃገሪቱ የኢነርጂ አቅርቦት ክፍተት በስፋት ጎልቶ የሚታው በገጠሩ የማህበረሰብ ክፍል እንደመሆኑ መጠን ይህንን ችግር ለሚቀርፉ የግል አልሚዎችን ለማሳተፍ በሚሰሩ ስራዎች የብድር አቅርቦቱን ለማሳለጥ እንዲቻል በሙያዬ የበኩሌን ሚና እንድወጣ ስልጠናው አግዞኛል ብለዋል፡፡
በተለይም በዘርፉ ላይ መልካም ተሞክሮ ያላቸው ሃገራት ልምዶች እና የጥናት ሰነዶች መቅረባቸው የሚበረታታ ሆኖ በዚሁ ዙሪያ የሚዘጋጁ ፖሊሲዎችና አዋጆች ቢጠናከሩ ደንበኞች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ ብለዋል፡