የንጋት ሀይቅ ለቀጣዩ ትውልድ በቅብብሎሽ የምናስረክበው በረከት ነው። ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ

የንጋት ሀይቅ ለቀጣዩ ትውልድ በቅብብሎሽ የምናስረክበው በረከት ነው። ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ቢሾፍቱ:- ጥቅምት 04/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የታላቁ ህዳሴ ግድብ-ንጋት ሀይቅ ረቂቅ ማስተር ፕላን ዙሪያ በሚደረገው የውይይት መድረክ ላይ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ባደረጉት ንግግር የንጋት ሀይቅ ለቀጣዩ ትውልድ በቅብብሎሽ የምናስረክበው ትልቅ በረከት ነው ብለዋል። የህዳሴ ግድብን የውሃ ሀብት በፍትሃዊነት መጠቀም የሚቻል መሆኑን የገለፁት ክቡር ሚኒስትሩ አሁን ያለው ትውልድና አመራሩ ዓባይን የኢትዮጵያ ኩራት እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል። በግድቡ ላይ የተፈጠረው የንጋት ሰው ሰራሽ ሀይቅ ከአፍሪካ 4ኛው ግዙፉ ሀይቅ በመሆኑ ለሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው ብለዋል። ለታሪክ የሚተላለፍ አሻራ የምናስቀምጥበትና ከትውልድ ወደ ትውልድ የምናስተላልፈውን ረቂቅ ማስተር ፕላን ዙሪያ በጋራ በመምከር ለውጤታማነቱ በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል። ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘውም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኛ አልፎ ለጎረቤት ሀገራትም በረከት የሚሆነው በጋራና በፍትሃዊነት ስንጠቀም መሆኑንም አክለው ገልጸዋል። የንጋት ሀይቅ ረቂቅ የማስተር ፕላን ቀድሞ የተዘጋጀ ቢሆንም በተበታተነ አግባብ ከሚመራ የበለጠ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በመሆን ረቂቅ ፕላኑን በማዳበር ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያለመ መድረክ አዘጋጅተናል ብለዋል። በንጋት ሀይቅ ዙሪያ ውሃውን በዘላቂነት ለማስተዳደር የሚያስችል ስራ ለመስራት እና ቅንጅታዊ አሰራርን ተግባራዊ ለማድረግ የባለድርሻዎች ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ከተሳታፊዎች የሚገኘው ግብዓት የዘርፉን ስራ የበለጠ ለማዳበር ስለሚያግዝ ሁሉም በንቃት እንዲሳተፍ አሳስበዋል። ሚዲያዎችም ህዳሴን በህዳሴ ልክ በመዘገብ እንደ ሀገር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ስራ እየተሰራ እንደሆነ እንዲያስገነዝቡ ክቡር ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል። በመድረኩ የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ ክቡር ዶ/ር አወቀ ሃምዛ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ጌታሁን አብዲሳ እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

Share this Post